ዶንጋ
የዶንጋ ብሔረሰብ
የዶንጋ ብሔረሰብ በከምባታ ጠምባሮ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ነው፡፡የብሄረሰቡ የህዝብ ቁጥር መ/ኢ/ክ ፕላን እና ልማት ቢሮ 2017 ዓ.ም ፕሮጄክሽን ወንድ 29,309 ሴት 28,555 በድምሩ 57,864 ነዉ፡፡ ብሔረሰቡ በዞኑ ከሚገኙት ወረዳዎች መካከል በዋናነት በሀደሮ ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ከዚህም ባሻገር ብሔረስቡ በዞኑ ካሉት ወረዳዎች መካከል በቃጫ ቢራ፤ በአንጋጫ፣ በቀዲዳ ጋሜላ እና በጠምባሮ ልዩ ወረዳዎች የብሔረሰቡ አባላት እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ እንዲሁም ከዞኑ ውጪ በወላይታ ዞን በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ፣ በሀዲያ ዞን በዱና በሶሮና በሆሳዕና ከተማ ዙሪያ በሀይሴ አካባቢዎች ከሌሎች የብሔረሰብ አባላት ጋር ይኖራሉ፡፡ ብሔረሰቡ በዋናነት በሚኖርበት አካባቢ የከምባታ፡ የጣምባሮና የወላይታ ብሔረሰብ አባላትም ተሰባጥረው በመተሳሰብና በመፈቃቀር ይኖራሉ፡፡ብሔረሰቡ የሠፈረበት መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ ተራራማ፣ ሸለቋማ እና ሜዳማ ሲሆን፤ የአየር ንብረቱም ደጋማ፣ ወይናደጋ እና ቆላማ ነው፡፡
ጥምር ግብርና የዶንጋ ብሔረሰብ ዋነኛ መተዳሪያው ነው፡፡ በአካባቢው ከሚመረቱት ምርቶች መካከል በቆሎ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ አተር፣ ባቄላ፣ ማንጐ፣አቡካዶ፣ ብርቱካን፣ ሙዝ፣ ፓፓዬ፤ ጐደሬ፣ ድንች / ሁለቱም ዓይነት/ "ቦዬ”ና እንሰት ተጠቃሾች ናቸው። ምርቶቹም በተለያየ ደረጃና መጠን ለፍጆታ እና ለገበያ ይመረታሉ፡፡ በተለይ ቡና እና ዝንጅብል ለገበያ ሲባል የሚመረቱ ከመሆናቸውም ባሻገር የብሔረሰቡ ዋነኛ የገቢ ምንጮች ናቸው።
ቋንቋ
የዶንጋ ብሔረሰብ "ዶንጊሳ˚ የሚባል ቋንቋ እንዳላቸው የብሔረሰቡ መረጃ ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው የሚነገሩ የሌሎች ብሔረሰቦች ቋንቋዎችን ማለትም ከምባትኛን፣ ሀዲይኛን፣ ዎላይታኝንና አማርኛን ለመግባቢያነት ይጠቀማሉ፡፡ ቋንቋዉን ለማልማት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን በባህልና ታሪክ ረገድ በባህልና ቱሪዝም ቢሮ በዶንጋ ብሔረሰብ ዙሪያ ጥናት ተጠናቆ አገልግሎት ላይ ዉሏል፡፡
ታሪካዊ አመጣጥና አሠፋፈር
የዶንጋ ብሔረሰብ ጥንተ-አመጣጥ ከሰሜኑ አገራችን ክፍል ከቀድሞው በጌምድር/ጐንደር/ አካባቢ በመንቀሳቀስ እንደሆነ የብሔረሰቡ ትውፊት ያስረዳል፡፡ ለእንቅስቃሴአቸው ዋናው ምክንያትም በአካባቢው በጊዜው የነበረው ጦርነት እንደነበርይገልፃሉ፡፡ ከቀድሞው ቦታቸው ተነስተው ወደ ደቡብ ሲጓዙም በዛሬው ጉራጌ ዞን ውስጥ እዣና ወለኔ አካባቢ ለተወሰኑ ጊዜያት ቆይታ እንዳደረጉ፤ ከዚያም የተወሰነው ክፍል ወደ “ዋስራ” “ሲሞዳ” እና “ሴች ዱና” በሚባሉ ሥፍራዎች ከቦሃቶራ” ተራራ መዳረሻ አካባቢ እንደሠፈሩ የዕድሜ ባለፀጋዎች ያስረዳሉ፡፡
ባህላዊ አስተዳደር
በዶንጋ ብሔረሰብ ሦስት የባህላዊ አስተዳደር እርከኖች አሉ፡፡ እነሱም፦ “ወማ” ንጉሥ የመጋባ ጉባኤ” እና “መጋባ" በሚል የማዕረግ ስም ይታወቃሉ፡፡ “ወማ” ከፍተኛው እና የመጨረሻው የሥልጣን እርከን ነው፡፡ ሥልጣኑም በዘር አአባት ወደ ልጅ ይተላለፋል። “ወማው ሲሞት ከወንድ ልጆቹ የማስተዳደር ብቃት ያለው ተመርጦ እንዲነግስ ይደረጋል። ወንድ ልጅ ከሌለው የ“ወማው" ወንድም እንዲወርስ ይደረጋል ።
የንግሥና ሥርዓቱ በባህላዊ ጭፈራ ይከበራል። የሴቶች ምርቃት “የወራሽን የአዲሱን “ወማ”/ የሥልጣን ዘመን ያስረዝማል፤ ዘመኑም የሠላም፣ የደስታና የጤና ዘመን እንዲሆን ያደርጋል" ተብሎ ስለሚታመን ለዚህ ተግባር የሚሆኑ ከ2-4 የሚደርሱ ሴቶች ይመረጣሉ፡፡ በዕለቱም ወለላ ማር ይዘው ከወራሹ ግራና ቀኝ ይቆማሉ፡፡ ከያዙት ወለላ ማርም ከቀንድ በተሠራ ማንኪያ ወራሹን ተራ በተራ እያቀመሱት "ንጉሥ ሆይ! ዘመንህ የተመቸ ይሁን! ክፉውን ያርቅልህ! የረገምከው የተረገመ፣ የመረቅከው የተመረቀ ይሁን!
ከዛሬ ጀምሮ ንጉሥ ነህና ጉንጭህ ሳይሆን እጅህ ይሣም!...” በማለት ይመርቁታል። ምርቃቱ እንዳበቃም የንግስና ምልክት የሆነው ቀለበት በከብት ደም ታጥቦ እና በቅቤ ታሽቶ እጣቱ ላይ ይደረጋል- ንጉሥ ሆነ፤ ህዝቡን የማስተዳደር ሥልጣኑን ተረከበ ማለት ነው፡፡ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ንጉሥ ምንም ዓይነት ሥራ እንዲሠራ አይፈቀድለትም፤ እርሻም አያርስም፡፡ በመንገድ ያገኙት ሁሉ እጁን እየሣሙ ይመረቃሉ፡፡ እንደ አስፈላጊነቱም ለንጉሱ የገንዘብ ስጦታም ያበረክቱለታል፡፡
ከወማ ቀጥሎ ያለው የባህላዊ አስተዳደሩ የሥልጣን እርከን “የመጋባ ጉባኤ” ሲሆን፤ በጥሩ ሥነ ምግባራቸው፣ በማስተዳደር ብቃታቸው፣ በዕውቀታቸው እና በዕድሜ አንጋፋነታቸው የተመረጡ የሀገር ሽማግሌዎችን ያቀፈ “የመማክርት ጉባኤ” እንደ ማለት ነው፡፡ የመጋባ ጉባኤ ቀጥታ ተጠሪነት ለወማ ይሆናል፡፡ “መጋባ” ተጠሪነቱ ለመጋባ ጉባኤ የሆነ ሦስተኛው የአስተዳደር ሥልጣን እርከን ነው፡፡ ሥልጣኑም በምርጫ የሚሰጥ እንጂ በዘር ሀረግ የሚተላለፍ አይደለም፡፡ በሌላ አገላለፅ “መጋባ” ከእያንዳንዱ ጐሣ /በብሔረሰቡ ወደ አስር የሚሆኑ ጐሣዎች እንዳሉ ይገመታል ብቃቱና ችሎታው እየታየ /እየተመዘነ/ የሚሰየም /የሚመረጥ/ የየጐሣው ሙሉ ውክልና የያዘ አስተባባሪ /የጐሣ መሪ/ ነው፡፡ በባህላዊ አስተዳደሩ እያንዳንዱ ጐሣ የየራሱ “መጋባ" የሚኖረው ሲሆን የሁሉም “መጋባ"ዎች ተጠሪነትም ለመጋባ ጉባኤ ይሆናል፡፡
በብሔረሰቡ አባላት መካከል በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ግጭቶች የሚፈቱት በመጀመሪያ የመዳኘት ሥልጣን ባለው የጐሣ መሪው /መጋባው/ነው፡፡ በእርግጥ ወደ መጋባው ሣይደርሱ በሠፈር ሽማግሌዎች የሚያልቁ ጉዳዮች አሉ፡፡ ችግሩ ከዚያ በላይ ሲሆን በመጋባ ደረጃ እንዲታይ ይደረጋል፡፡ ከዚህም በላይየሆነ እንደሆነ ደግሞ ለመጋባዎች ጉባኤ ቀርቦ ይታያል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ግጭቶች ቢከሰቱ ወይም በግጭቱ የሰው ነፍስ የጠፋ ከሆነ ጉዳዩ ለ “ወማው” ይቀርባል። “ወማውም" የመጨረሻ ውሣኔ ይሰጣል፡፡ በዳይ አጥፊው/ እንዲቀጣ፤ተበዳይ እንዲካስ ይደርጋል ።
ዳግመኛ በክፉ እንዳይፈላለጉም የ "ጉዳ" /ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓት/ ይፈፀማል፡፡ ሥርዓቱ የሚፈፀመውም ጥቁር እና ዳለቻ ክብት በማረድ በታረደው ከብት ደምም ሁለቱም ወገኖች እጃቸውን እንዲታጠቡ እና መሬት የፈስስውን ደም እየረገጡ እንዲራመዱት በማድረግ ነው። ይህ ባህላዊ ሥርዓት እስከ ዛሬ እንደሚተገበርየአካባቢው አዛውንቶች ይናገራሉ፡፡በብሔረሰቡ ዘንድ ሴቶች በባህላዊ አስተዳደርውስጥ ያን ያህል የጐላ ሚና የላቸውም። ይሁን እንጂ "ሴት የመረቀችውም ሆነ የረገመችው መሬት ጠብ አይልም- ይደርሣል” ተብሎ ስለሚታመን ሴቶች ይከበራሉ፡፡ ትልቅ ሥፍራም ይሰጣቸዋል፡፡
እንዲሁም "ሴት የመረቀችው ሁሉም ነገር ይበረክታል" ተብሎ ስለሚታመን በብሔረሰቡ የከብት ቆጠራ ሥርዓት” ወቅት ወይም በጋብቻ ሥርዓት ወቅት ተጋቢዎችን በሴት እህቶቻቸው ማስመረቅ የተለመደ ነው፡፡ መራቂዋ ሴትም ከምርቃቱ በኋላ ልብስ፣ ገንዘብ፣ ማር ይሰጣታል፡፡ እንዲሁም በከብት ቆጠራ ሥርዓት ከምርቃቱ በኋላ የፈለገችውን ከብት መርጣ የመውስድ መብት አላት፡፡ ለጥሩ ነገር የሴት ልጅ ምርቃት ትልቅ ግምት የሚሰጠውን ያህል “ሴት ልጅ ከረገመች እርግማኑ ይደርሳል" ተብሎ ስለሚታመን በብሔረሰቡ የሴት እርግማን በጣም ይፈራል፡፡ ስለዚህ የማህበረሰቡን ወግና ልማድ የሚጥስ ወይም የሚተላለፍ በሴቶች እንዲረገም የሚደረግበት አጋጣሚ ስለሚኖር ክፉ አድራጊ ከድርጊቱ ይታቀባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የንጉሥ ሚስትም “ቃርቾተ" /ንግሥት/ በብሔረሰቡ ትልቅ ክብርና ሥፍራ ይሰጣታል፡፡ ለንጉሡ የሚሰጠው ክብር ለእሷም ይሰጣታል፡፡ በአጠቃላይ በዶንጋ ብሔረስብ ለሴቶች የሚሰጠው ቦታ ወይም በብሔረሰቡ የሴቶች ሚና ቀላል አለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
በብሔረሰቡ ዘንድ ከአስተዳደራዊ መዋቅር ወጣ ብሎ መንፈሣዊ ጉዳዮች የሚያስፈጽሙ አባላት አሉ፡፡ አሁን የክርስትና ኃይማኖት በመስፋፋቱ እየቀረ መጣ እንጂ፣ ጥንት በዶንጋ ብሔረሰብ ውስጥ የ “ቃይደራ” /የቃልቻ/ እምነት ተከታዮች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ይህ የ“ቃይደራ” እምነት የተጀመረውና የሚመራው “ሃp” በተባለ ጐሣ ሲሆን፤ ትርጉሙም “የአምላክ ልጅ" እንደማለት ነው፡፡ “መ " /ቃይደራ አማካሪ/ እና 'ሞሮታ" /አገልጋይ/ የሚባሉ ሁለት የአስፈፃሚ አካላት አሉት፡፡ በዚህ የ "ቃይደራ" /የቃልቻው/ የመኖሪያ ሥፍራ የሚዘጋጀው በደን በተሸፈነ ጫካ ውስጥ ሲሆን ሥፍራውም “ፈዱ" በመባል ይታወቃል፡፡ “ቃይደራ” ከእምነት ሥራ ጐን ለጐንም የወማዉ" /የንጉስ/ አማካሪ ሆኖ ይሠራል፡፡
የዚህ እምነት ተከታዮችም “ቀይደራ" አንድ ኃይል ያለው የሁሉም አምላክ መሆኑን፣ ይህም አምላክ የመላውን ሰብአዊ ፍጡር ህይወት በቅርበት እንደሚከታተል፤ ከጠላት እንደሚታደጋቸው፤ ከረሃብና ከበሽታ እንደሚጠብቃቸው፤ እንደሚያዘንብላቸው፤ ስለሚያምነ ያከብሩታል። አስፈላጊውን ሁሉ ይፈፅሙለታል፡፡ ዝናብ ተገቢው ሁሉ ካልተፈፀመለት ግን “ቆሌው ይቆጣል፤ ከተቆጣ ደግሞ በበሽታ፣ በረሃብ... በአጠቃላይ ሰውን በተለያየ መንገድ በማሰቃየት ይቀጣል..." ተብ ስለሚታመን ለሥርዓቱ ትልቅ ሥፍራ ይሰጡታል፡፡ በዚህም የተነሣ የእምነቱ ተከታዮች ከእርሻ ምርታቸው ወይም ካላቸው ሀብት የመጀመሪያውን ለ “ቃይደራ ይሰጣሉ፡፡
ባህላዊ ዕሴቶች
የጋብቻ ሥርዓት
በዶንጋ ብሔረሰብ አሁንም ያሉና የሚዘወተሩ 5 የጋብቻ ዓይነቶች ሲኖሩ፤ እነሱም፡-“ቆሮሲሻታ” /በወላጆች ስምምነት የሚፈፀም ጋብቻ/ “ሚዱ” /የጠለፋ ጋብቻ/፡ “ላበቱታ” /ሴቷን በሦስተኛ ወገን በማታለል ወይም በማባበል የሚፈፀም ጋብቻ/“ሄሩ” /በተጋቢዎች ስምምነት የሚፈፀም ጋብቻ/፣ እና “ራጊታ” /የውርስ ጋብቻ/በመባል ይታወቃሉ፡፡ ከሁሉም በስፋት የሚዘወተረው “ቆርሲሻታ” የሚባለው የጋብቻ ዓይነት ሲሆን፤ አፈፃፀሙም የብሔረሰቡን ባህልና ወግ ተከትሎ በወላጆች በጐ ፍቃድ ላይ ተመስርቶ በሠርግ የሚፈፀም ጋብቻ ነው፡፡
የጠለፋ ጋብቻ /ሚዱ/ ልጅቷም ሆነች ወላጆቿ ሣይፈቅዱ በአግቢው ፍለጐት ብቻ በኃይል የሚፈፀም ጋብቻ ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ጋብቻ እንደ ምክንያት ከሚቆጠሩት መሃል የአግቢው የኢኮኖሚ አቅም ዝቅተኛ መሆን የዘር አቻ አለመሆን... ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ ጋብቻ አሁንም በብሔረሰቡ ዘንድ እንደሚፈፀም ይነገራል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ጋብቻ ወቅት ልጃቸውን በሚያስጥሉትና በጠላፊዎች መካከል በሚደረገው ግብግብ ከፍተኛ ግጭት እንደሚከሰት የብሔረሰቡ አባላት ይገልፃሉ፡፡
የማባበል "ላበቱታ” የሚባለው ጋብቻ አፈፃፀሙ ልጅቷን በ3ኛ ወገን በማባበል እና ከልጁ ጋር በማገናኘት የሚፈፀም ጋብቻ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ጋብቻ ልጁና ልጅቷ በደንብ ከተዋወቁና ከተጠናኑ በኋላ ልጅቷ ለወላጆቿ ሣታሣውቅ ከቤት አንድ የሆነ ነገር ይዛ ትሰወራች። በተያዘላት ቀጠሮም ተደብቃ ወንዱ ቤት ትሄዳለች፡፡ የዕቃውን መጥፋት ወላጆቿ ሲያውቁም ልጃቸው ማግባቱን ይረዳሉ፡፡ የወንዱ ወገኖችም በሦስተኛው ቀን ወደ ሴቷ ወላጆች ልጃችሁ እኛ ዘንድ ናት” በማለት ሽማግሌ ይልካሉ፡፡ አስፈላጊው ሁሉ ተፈፅሞ ጋብቻው እንዲፀና ይደረጋል፡፡
ሜሩ" በሁለቱ ተጋቢዎች ስምምነት የሚፈፀም የጋብቻ ዓይነት ነው። በዚህ ዓይነቱ ጋብቻ ሁለቱም ፍቅረኛሞች በሚያደርጉት ስምምነት ተያይዘው በመጥፋት ከወላጆቻቸው ርቀው ይደበቃሉ፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ በሚልኩት ሽማግሌ ጉዳዩ አልቆ ጋብቻው ይፈፀማል።
የውርስ ጋብቻ /ራጊታ/ የሚባለው ባል ሲሞት የባል ታናሽ ወንድም ወይም የቅርብ ዘመድ የሟችን ሚስት የሚያገባበት የጋብቻ ዓይነት ነው፡፡ አላማውም የወንድሙን ልጆችና ሀብት ለመንከባከብ ሲባል ነው፡፡ የጋብቻ ሥርዓቱ ከመፈፀሙ በፊት የሟች ሚስት ፈቃደኝነት ይጠየቃል፤ ፍቃደኛ ካልሆነች አትገደድም። በዚህ ሥርዓት መሠረት የሟች ባሏን ታናሽ ወንድም ያገባችው ሴት ለአግቢው እንደ ህጋዊ ሚስት አትቆጠርም። የሚወለዱ ልጆችም የሚጠሩት በሟች ስም እንጂ በወራሽ ስም አይደለም፡፡
በእነዚህ በተጠቀሱት መንገድ /ከውርስ ጋብቻ በስተቀር/ ለሚፈፀሙ ጋብቻዎች የሚቀርበው ጥሎሽ በሁለት ደረጃ ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው ጥሎሽ “አፌ ፈና” /አፍ መክፈቻ/ የሚባለው ሲሆን ከብር 300 እስከ ብር 5ዐዐ እንዲሁም አንድ እንስራ ማርይሰጣል፡፡ ሁለተኛው የልጅቱ ወላጆች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት በገንዘብ እና በዕቃ መልክ የሚስጥ ጥሎሽ ነው፡፡ የገንዘብ መጠኑም ከብር 500 እስከ ብር 1000 የሚደርስ ሲሆን ለእናት፣ ለአባት፣ ለወንድምና ለእህት እንዲሁም ለሙሽራዋ የሚሆን ልብስ በዓይነት ይቀርባል፡፡ በዚህ የጥሎሽ ሥርዓት የእናት ድርሻ ከፍ ያለ ነው፡፡ በብሔረሰቡ በድሮ ጊዜ ይሰጥ የነበረው የጥሎሽ መጠን ከፍተኛ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን ያ ሁሉ ቀርቶ የወንዱን አቅም ባገናዘበ መልኩ በስምምነት ያልቃል።
በዶንጋ ብሔረሰብ በወላጆች ስምምነት በሚፈፀም ጋብቻ ወቅት ወንዶች ከጋበቻቸው በፊት እንዲገረዙና በደንብ እንዲቀለቡ ይደረጋሉ፡፡ ሴት ልጅ ደግሞ የምትገረዘው ልክእንደታጨች ነው፡፡ የታጨችና የተገረዘች ስለመሆኗም አናቷ መሀል ክፍት የሆነ እንድታሣድማ ሹሩባ ትሠራለች። እንዲሁም ሴት ልጅ ከተገረዘች በኋላ የእጅና የእግር ጥፍሮቿን እንድታሳድግ ፈቀድላትም፡፡ ምክንያቱም በሠርግዋ ዕለት /ጫጉላ ቤት ውስጥ በሚከናወነው ሥርዓት ወቅት ወንዱን በጥፍሮቿ እንዳትባጭረው በማሰብ ነው፡፡
ባህላዊ በዓላት አከባበር
በዶንጋ ብሔረሰብ በየዓመቱ የመስቀል በዓል ይከበራል፡፡ የመስቀል በዓል አከባበር በብሔራዊ ደረጃ አንደሚከበረው እለቱን ጠብቆ መስከረም 17 ቀን ሳይሆን ለመስከረም 17 በሚቀርበው ቅዳሜ ዕለት ነው፡፡ ቀኑ ለቅዳሜ የተጠጋ ቅርበት ካለው ወደፊትም ሆነ ወደ ኋላ ያለውን ቅዳሜን በማስላት ይክበራል፡፡ በመስቀል ዋዜማ የመስቀል ገበያ ተብሎ በማለዳ ይቆማል፡፡ የመስቀል ሰንጋም በየቄየው ይዘጋጃል። የመጀመሪያው ሰንጋ የሚጣለው /የሚባረከው/ በወማው /በንጉሱ/ ደጃፍ ሲሆን የዚህ ክንውን ለማህበረሰቡ በነጋሪት ይበሰራል፡፡ ከዚያም ሁሉም በየደጃፉ ዕርዱን ይፈጽማል፡፡ የመስቀል ዕለት ዋዜማ ዐርብ "የአተካኒ ሐረባ" የአታካና አርብ ተብሎ በዋዜማው ልዩ ዝግጅት ይደረጋል፡፡ በዚህ እለት ከቆጮ፣ ከወተት እና ከቅቤ የሚሠራ "አተካኒ" የሚባለው ምግብ ይበላል፡፡ በሶስተኛው ቀን ሕዝቡ "ጊፋታ የሚባል ባህላዊ ጨዋታ እየጨፈረ ወማን እያሞገሰ ወደ ወማው መኖሪያ ይሄዳል፡፡ ንጉሱም ሕዝቡን መርቆ ለቀጣዩ መስቀል በሰላም ያድርሰን የሚል ምኞቱን ገልፆ ይሸኛል፡፡ ሌላው ባህላዊ በዓላቸው ፋሲካ ሲሆን በዕለቱ ከጤፍ ዱቄት ተለውሶ በቅጠል ተጠቅልሎ የሚሠራ ቅቅል "ኡድርገፎ" የሚባል ምግብ ለበዓሉ ድምቀት እና ክብር ተዘጋጅቶ ይበላል፡፡
የባህላዊ ቤት አሠራር
የብሔረሰቡ ባህላዊ ቤት ክብ ሆኖ ግድግዳው ከእንጨት፤ ክዳኑ ከሣር ይሠራል። ቃጫ እና "ጡሾ˚ /ገመድ/ ደግሞ ለማሠሪያነት ያገለግላሉ፡፡ በቤቱ ሥራ በአብዛኛው ወንዶች የሚሣተፋ ቢሆንም ሴቶችም መጠነኛ የሆነ የሥራ ድርሻ አላቸው።የቤቱ ሥራ የሚከናወነው በደቦ ሆኖ እንጨት ከዱር ቆርጦ ማቅረብና የቀረበውን እንጨት መፍለጥ፣ ለክዳን የሚሆን ሣር ማጨድ እና የቤቱን ሥራ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ማከናወን የወንዱ ድርሻ ሲሆን ለክዳን የታጨደውን ሣር ማጋዝ፣ ለማሠሪያ የሚሆነውን ቃጫና ጡሾ፣ ምግብና መጠጥ ማዘጋጀት ደግሞ የሴቶች ድርሻ ነው፡፡
ባህላዊ የመገልገያ መሣሪያዎች
የብሔረሰቡ አባላት ለቤት ውስጥ መገልገያ፣ ለእርሻ ሥራ፣ ለአደን፣ ለጦርነት፣ ለሙዚቃ እና ለጌጣጌጥነት የሚውሉ ቁሳቁሶች ከእንጨት፣ ከቀርከሃ፣ ከሸክላ ከድንጋይ እና ከሌሎችም በአካባቢው ከሚገኙ ጥሬ ሀብቶች በመሥራት ይጠቀማሉ፡፡ ለአብነት "ቡሌ/ የቅል መጠጫ፣ "ጋያ" የትንባሆ መሣቢያ፣ መጅና ወፍጨ፣ ወንፊትና፣ ዋንጫ፣ ጡሩምባ፣ ቡልኮ፣ ጦር፣ ጋሻ፣ ጐራዴ፣ የእንጨት ትራስ የሽክላ ሲኒና ሌሎችም ከላይ በዝርዝር ከተጠቀሱት ጥሬ ሀብቶች በመሥራት ይገለገሉባቸዋል፡፡
ባህላዊ ምግብ
እንስትና የእንሰት ውጤቶች /ቆጮ፣ ቡላ፣ሙቾ ፤አታካኖ፣ ስኳር ድንች፣ ጐደሬ፣ ገንፎ፣ በብሔረሰቡ ዘንድ የሚዘወተሩ ባህላዊ ምግቦች ናቸው፡፡ በተለይም “አታካኖ የሚባለው ምግብ የብሔረሰቡ ተወዳጅ ምግብ ነው፡፡ የሚዘጋጀው ከቆጮ ከወተትና ከቅቤ ሲሆን ብዙውን ጊዜ የሚዘጋጀው በመስቀል በዓል በመጀመሪያው ዓርብ ቀን ተዘጋጅቶ በእለቱ ይበላል፡፡
ባህላዊ አለባበስ
የብሄረሰቡ አዛውንቶች ተነፋነፍ ሱሪና እጀ-ጠባብ ሱሪ መልበስ ሲያዘወትሩ በጣታቸው የብር ቀለበት ያደርጋሉ፡፡ እናቶች ደግሞ ክጥጥ ፈትል የተሠራ ቡልኮ አጣጥፈው በማገልደም ይለብሳሉ፡፡ ወጣት ወንዶች ለአቅመ አዳም ሲደርሱ ተነፋነፍ ሱሪና እጀ-ጠባብ፣ ታዳጊ ልጆች የበግ ወይም የፍየል ለምድ ከጀርባቸው በማንጠልጠል ይለብሣሉ፡፡ ልጃገረዶች ደግሞ “ቂጦታ" /Qexata/ የሚባል የተለፋ እና በቅቤ የወዛ የበግ/የፍየል/ አጭር ለምድ ይለብሱ እንደነበርና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ አለባበስ በአብዛኛው በዘመናዊ አለባበስ እንደተተካ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ የዶንጋ ወማ/መሪ/ የነብር እና የአንበሣ ቆዳ በልዩ ጌጥ ተሠርቶ ሲለብሱ የወማ ሚስት "ቃርቹታ" ጉሜ የሚባል አንባር በእÍ ወይም በአንገቷ ታደርጋለች፡፡
የለቅሶ ሥርዓት
በዶንጋ ብሔረሰብ አንድ ሰው ሲሞት እንደሟቹ ዕድሜ እና ማህበራዊ ደረጃ ሥርዓተ-ሀዘኑም ሆነ ሥርዓተ-ቀብሩ ይለያያል፡፡ ህፃን ሲሞት ወዲያው ሥርዓተ ቀብሩ ይፈፀማል፡፡ ለአዋቂ ቀበርነው የሚባለው ቋንቋም አጠፋነው ወደሚለው ፈሊጣዊ አነጋገር ይለወጣል፡፡ ወጣት ሲሞት ሥርዓተ- ቀብሩና ሥርዓተ ለቅሶው በአንድነት ይፈፀማል፡፡ የሞተው አዋቂ ሰው ከሆነ ደግሞ ቀብሩ የሚፈፀመው ከሦስት ቀን በኋላ ነው፡፡ አስክሬኑ እንዳይሸትም በጨው ውኃ ይታጠባል፡፡ የለቅሶ ሥርዓቱ የቀብሩ ዕለት አሊያም በሌላ ቀን /በቀጠሮ/ ሊፈፀም ይችላል፡፡ ከ3 ቀን በኋላ የመቀበሩ ምስጢርም ርቀው የሚገኙ ዘመዶች ከመቀበሩ በፊት ደርሰው የሟቹን አስከሬን ማየት ስላለባቸው ነው ይባላል፡፡
የባህላዊ አስተዳዳር መሪው /ወማው/ ንጉሡ የሞተ እንደሆነ አይለቀስም፤ ሞቱም ወዲያው ለሕዝቡ አይገለፅም፡፡ “ንጉሡ ጠፉ" /ወሙ በኤማ/ እየተባለ ለሁሉም የጐሣ መሪዎች /ለመጋባዎች/ እና ለአገር ሽማግሌዎች መልዕክት በድብቅ ይተላለፋል፡፡ መልዕክቱ የደረሳቸው “መጋባዎች" እና ሽማግሌዎችም ወዲያውኑ ይሰበሰቡና ስለ ቀብሩ እና ስለ ንግሥና ሥርዓት፤ እንዲሁም ስለ ሌሎች ቅድመ-ዝግጅቶች በጋራ ይመክራሉ፡፡ አስክሬኑ አስከሚቀበር እና አዲስ ንጉስ እስከሚነግስ ድረስም ሽማግሌዎቹ እህል ውኃ አይቀምሱም። የቀብሩም ሆነ የንግሥናው ሥርዓት በሁለተኛው ቀን በአንድነት ይከናወናል፡፡ በዕለቱ ከብት ይታረዳል፤ እህል ውኃ ይዘጋጃል፤ አስክሬኑ በታረደው የከብት /እርጥብ/ ቆዳ ተገንዞ፤ በቡልኮ ተከፍኖ፤ መቃብሩ በደምና በማር ታጥቦ ሁሉም የጐሣ መሪዎች በተገኙበት የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ በ2ኛው ቀን ማታ ላይ በድብቅ ይፈጸማል፡፡ ይህ ሲሆን አይለቀስም አይታዘንምም። ከጐሣ መሪዎች ውጭ ሌሎች የማህበረሰቡ ክፍሎች በቀብሩ ሥፍራ አይገኙም። ይህ እንደተጠናቀቀም ወዲያው የወራሹ ንጉሥ /ወማው/ የንግሥና ሥርዓት ጠማ ሄ እና "ሄቦ ዩታ" በሚል ጭፈራ ታጅቦ ይፈፀማል። ይህ ሲሆንም የተቀረው የማህበረሰብ አባላት የቀድሞው ንጉሥ መሞቱን እና በምትኩም አዲስ ንጉሥ መንገሡን ይረዳሉ፡፡