የም
የየም ዞን አጠቃላይ ገጽታ
የየም ዞን በክልሉ ከሚገኙት 7 ዞኖችና 3 ልዩ ወረዳዎች መካከል አንዱ ሲሆን በ1 ከተማ አስተዳደር፣በ3 ወረዳ፣በ32 የገጠርና በ7 የከተማ ቀበሌዎች የተዋቀረ ነው፡፡ዞኑ በሰሜን በደቡብና በምዕራብ ፡ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ሲዋሰን በሰሜን ምስራቅ እና በምስራቅ ደግሞ ከጉራጌ እና ከሀዲያ ዞኖች ጋር ይዋሰናል ፡፡ የዞኑ መልካ ምድራዊ አቀማመጥ ተራራማና ከፍል ወጣ ገባነት የሚበዛበት ሲሆን የአየር ንብረቱም በአብዛኛው ደጋና ወይና ደጋ ሆኖ በከፊል ቆላማ ነው፡፡ሣጃ የዞኑ ዋና ከተማ ነዉ፡፡በ1999 ዓ/ም በተካሄደው የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ ውጤት መስረት የልዩ ወረዳው አጠቃላይሕዝብ ብዛት 138,759 ነው:: በ2017 ዓ.ም ማ/ኢ/ክ የፕላን እና ልማት በተደረገዉ ፕሮጄክሽን መሠረት ወንድ 63,017 ሴት 62,910 ድምር 125,926 እንደሚሆን ይገመታል፡፡
በየም ዞን የተለያዩ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ መስህቦች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል የአንገሪ ቤተመንግስት ፣የዞፍካር ትክል ድንጋይ፣የመሊሳ ትክል ድንጋይ፣የፎፋ መድሃኒአለም ቤተክርስቲያን፣የቻሎ ባህላዊ ዳኝነት፣የቦር ተራራ፣ የኩሙል ጥብቅ ደን፤ የብርብርሣ ፏፏቴ፣ዎማ ፍል ዉሃ፣የጥቅምት 17 ባህላዊ መድኃኒት ለቀማ የሰሙ አዋሾ ሰዉ ሰራሽ ዋሻዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የየም ብሔረሰብ
የየም ብሔረሰብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ውስጥ ከሚገኙ 10 ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ ብሔረሰቡ በዋናነት በዞኑ የሚኖር ሲሆን በጉራጌና በሃዲያ ዞኖች ውስጥም ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በስብጥር ይኖራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርካታ የብሔረሰቡ አባላት በኦሮሚያ ክልል በጂማ ዞን ውስጥ ይኖራሉ፡፡
የብሔረሰቡ ዋነኛ የኢኮኖሚ መሰረት ጥምር ግብርና ነው፡፡ በግብርና ምርቶች ረገድ የተለያዩ የጥራ ጥሬ የሥራ ስርና የፍራፍሬ ምርቶች የሚመረቱ ሲሆን ከነዚህም መካከል እንሰት፣ ገብስ፣ ስንዴ፤ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ባቄላ፣ አተር፣ አደንጓሬ ፣ ምስር፣ኮክ፤ ሙዝ፤ አቡካዶ፣ ማንጐ፤ ፓፓያ ፤ ጐደሬ፣ ስኳር ድንች እና ቦይና ቆጪኖ/ ተጠቃሾች ናቸው ፡፡ ከእርሻ ስራው ጐን ለጐን የከብት እርባታና የእደ ጥበብ ሥራዎችን በማከናወን ኑሮውን ይደጉማል፡፡
ቋንቋ
በምስራቅ ኦሞአዊ የቋንቋ ቤተሰብ ሥር የሚመደበው "የምሣ" የብሔረሰቡ አፍ መፍቻ ቋንቋ ነው፡፡ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የብሔረሰቡ አባላት ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ ጉራጊኛን፣ ሃዲይኛንና ኦሮምኛን በተለያየ ደረጃ ይጠቀማሉ፡፡ ቋንቋው ከዳውሮ ፤ ከካፊቾ፣ ከወላይታ፣ ከቤንች፣ እና ከሽኮ ብሔረሰብ ቋንቋዎች ጋርበአነጋገር ዘይቤና በቃላት ይቀራረባል፡፡ ቋንቋውን ለማሣደግ በመንግሥት በኩል ከተደረጉ ጥረቶች ውስጥ ለአብነት የሚጠቀሰው በቀድሞዉ በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተጠናው የየምሳ ቋንቋ ሰዋሰው(2005 ዓ.ም)፣ የየም ብሔረሰብ ስነ ልሳኖች በአቶ ምስጋና ክበደ (2008 ዓ.ም)፣ የቻሎ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት በአምባሳደር ምትኩ ነጋሽ (2005 ዓ.ም)፤ የየም ብሔረሰብ ዘመናዊ ታሪክ በአቶ ምልኪያስ ለሚሶ (2008 ዓ.ም) የሚጠቀስ ሲሆን እስካሁን ቋንቋውን በተመለከተ ከመግባቢያነት ባለፈ የትምህርት መስጪያና የሥራ ቋንቋ ለማድረግ አልተቻለም፡፡
ታሪካዊ አመጣጥና አስፋፈር
ብሔረሰቡ ከሁለት የተለየዩ አቅጣጫዎች እንደመጣ ይነገራል፡፡ የአፈ ታሪክ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከየመን መጣ የተባለው ቡድን ከኢየሩሳሌም ፣ ከባቢሎን፣ ከሶሪያ እና ከመቄዶኒያ ተነስቶ የመን እንደገባ ከዚያም በባብኤል መንደብ አድርጐ ወደ ኢትዮጵያ / አሁን ወዳለበት አካባቢ / መጥቶ እንደሰፈረ ሲነገር በሌላ በኩል ደግሞ ባላአም ፤ ዋዝኖ፣ ጌሌማሽ፣ እና ፉጋ ቴስቶ /ፉጋቴስ/ የተባሉ አራት ወንድማማቾች ከጐንደር ተነስተው ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ተጉዘው የጉራጌን አካባቢ አቋርጠው እና የጊቤን ወንዝ ተሻግረው አሁን ካሉበት አካባቢ /የም / እንደደረሱ ይታመናል፡፡ ከዚያ ቀደም ሲል / እነዚህ ከመምጣታቸው በፊት/ ግን በየም አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ነባር የማህበረሰብ ክፍሎች ነበሩ ።
እነዚህ ቀደምት የአካባቢውን ነዋሪዎችም ገሚሱ በምስራቅ ገሚሱ በምእራብ ለሁለት ተከፍለው ይኖሩ ነበር፡፡ የምስራቆቹ "ኬላይምኖ" በሚባል "ታቶ" ንጉስ፤ የምዕራቦቹ ደግሞ " ኤሪኖ" በሚባል "ታቶ" /ንጉስ/ ይተዳደሩ ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ሲኖሩም ከላይየተጠቀሱት ሌሎች ወገኖች ከጐንደርና ከየመን መጥተው ተቀላቀሉዋቸው፡፡ ከዚያም ሁሉም ወገኖች እና ሕዝቦች በየም ምድር ላይ በሰላም እና በአንድነት መኖርጀመሩ፡፡ ባጠቃላይ በየም ብሔረሰብ ከ2ዐዐ በላይ ስያሜ ያላቸው ጐሣዎች እንዳሉ ሲገመት ስያሜያቸውም ከሙያ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ባህላዊ አስተዳደር
የብሔረሰቡ ባህላዊ አስተዳደር የየራሣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት ባላቸው 6 የሥልጣን እርከኖች የተከፋፈለ ነው፡፡ እነዚህም የሥልጣን እርከኖች "ታቶ" ፣ "ናንተስ' ፤ "አስተሰር"፣ “ኤራሾ"፣ "ጋኛ"፣ እና "ሸኒ" በመባል ይታወቃሉ፡፡ባህላዊ አስተዳደሩ በበላይነት የሚመራው በ"ታቶ" /ንጉስ/ ሲሆን ታቶ የሚመረጠውም ከ "ኮምዋ" ጐሣ ሆኖ ሥልጣኑም በዘር ሀረግ ከአባት ወደ ልጅ የሚተላለፍ ነው፡፡ 'ናንተስ˚ የስምንት ጐሣ ተወካዮችን የያዘ እና ከ'ታቶ" ቀጥሎ ያለ የአስተዳደር አካል ነው፡፡ ዋናው ተግባሩም አዲስ የሚሾመውን ታቶ /ንጉስ/ የማስተዳደር ብቃቱን እና ስነ ምግባሩን በመገምገም መሾም ወይም ማንገስ ነው፡፡ "አስተሰር" ሁሉም ጐሣዎች የተወከሉበት ሲሆን “ኤራሾ" /ቆሮ/ ደግሞ የንጉስ ተላላኪዎችን ወይም ጉዳይ አስፈጻሚዎችን ያቀፈ አካል ነው፡፡
በድሮ ጊዜ “ታቶ" ግዛቱን ከፋፍሎ ለኤራሾች ይሰጥ ነበር፡፡ እነሱም ተከፋፍሎ በተሰጣቸው በንጉሱ ግዛት ውስጥ ባለው ሕዝብ ላይ በጋኛ /በጭቃ ሹሞች/አማካኝነት ግብር ይሰበስባሉ፡፡ "ጋኛ" /ጭቃ ሹም/ በባህላዊ አስተዳደሩ ዝቅተኛ የሥልጣን አካል ሲሆን እንደ መንደር ሃላፊ ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ ከ"ጋኛ በታች ደግሞ "ሸኒ" ወይም "ናስጋኝ" የሚባሉና በየጐጡ በተላላኪነት ወይም በጉዳይ አስፈፃሚነት የሚያገለግሉ አካላት ይገኛሉ፡፡ የብሔረሰቡ አባላት የተጣላን የማስታረቅ፣ ሀይለኛውን የማብረድ፣ እምቢተኛውን የማግባባት፣ የቆየ ባህል አላቸው፡፡ በዚህ ባህላዊ ልማዳቸውም በማህበረሰቡ መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት በዳይን የመቅጣት እና ተበዳይን የመካስ ተግባር በማከናወን የማስታረቅ ሥራ ይሠራሉ፡፡
እንደ ግጭቱ አይነትና ደረጃ የዳኝነት አካሉ ይለያያል፡፡ ከበድ ያሉ ግጭቶች ሲከስቱ የሚታዩ ሲሆን ግጭቱ እንደተከስተ ንጉሱ አስተስሮችን በመሰብሰብ በጉዳዩ ላይ ያወያያቸዋል፡፡ ጉዳዩን በጥልቀት በመመርመር ጥፋተኛውን የመለየት ሥራ ይሰራሉ፡፡ በሥርዓተ ሕጉ መሰረትም ውሣኔ ሰጥተው በማስታረቅ ሁለቱ ወገኖች ለዳግም በቀል እንዳይነሳሱ መክረውና ገስፀው ያስናብቷቸዋል፡፡ ግጭቶቹ መለስተኛ ከሆኑ ደግሞ በተዋረድ ባሉ የአስተዳደር አካላት ወይም የጐሣ መሪዎች ወይም በአገር ሽማግሌዎች አማካይነት እንዲፈቱ ይደረጋል፡፡ የሞች ጥፋተኛውን የሚቀጡበት በርካታ የቅጣት አይነቶች ነበራቸው፡፡ እነዚህ ዓይን ያጠፋን አይኑን ፣ ጆሮ የቆረጠውን ጆሮውን ወዘተ ዓይነት ከበድና ጠንከር ያሉ ነበሩ፡፡ እንዲሁም የአጥፊውን እግሮች በኃይል በልቅጦ ከችካል ጋር በማሰር ማሰቃየት በወቅቱ ከሚፈፀሙ ቅጣቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው። የዚህ አይነቱ ቅጣትም በብሔረሰቡ ዘንድ "አባልበልሉ" በመባል የሚታወቅ ሲሆን ቅጣቱም ተፈፃሚ የሚሆነው ደግሞ ዝሙት በሚፈጽሙና በቤተ መንግሥት ውስጥ እኩይ ተግባርበሚፈጽሙት ላይ ነው፡፡ በጥፋተኛው ቁመት ልክ ጉድጓድ ቆፍሮ ጥፋተኛው ከአንገቱ በታች ቀብሮ በጭንቅላቱ እና በአካባቢው ጨው ነስንሶ ከብቶችን በመልቀቅ ማስረገጥ ከሁሉም ከባድ ቅጣት ነበር፡፡ ይህ የሚደረገው ከብቶቹ በጥፋተኛው ጭንቅላት እና በአካባቢው የተነሰነሰውን ጨው ለመላስ ወዲህና ወዲያ ሲራኮቱ ጥፋተኛውን ረጋግጠው እንዲገሉት በማስብ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በየሞች ባህላዊ አስተዳደር መዋቅር ውስጥ ከፆታቶ" ሚስት በስተቀር ሌሎች ሴቶች አንዳች ሚና እንዳልነበራቸው ይነገራል፡፡ የንጉስ ሚስት “ኤኖ" በሚል የማዕረግ ሥም የምትጠራ ሲሆን በብሔረሰቡ ዘንድም የንጉሱን ያህል ትከበራለች፡፡ ይሁን እንጂ በዳኝነት ሥርዓት ወቅት ባንዳንድ ጉዳዮች ላይ ንጉሱ ውሣኔያቸውን እንዲለውጡ ወይም ምህረት እንዲያደርጉ ከማማለድ በስተቀር የጐላ ተሳትፎ የላትም፡፡ ጥንት የየም ብሔረሰብ ማንነቱን እና ነፃነቱን ለመፈታተን የመጡበትን ጠላቶች ሲዋጋና ሲታገል መቆየቱን አንዲሁም ብሔራዊ ሕልውናውን ለማስጠበቅ ሲል ከፋሺሽት ኢጣሊያ ወራሪዎች ጋር ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉን አንዳንድ የታሪክመጻሕፍት ይገልፃሉ፡፡
ባህላዊ እሴቶች
የጋብቻ ሥርዓት
በየም ብሔረሰብ አምስት የጋብቻ ዓይነቶች አሉ፡፡ እነርሱም በቤተሰብ ስምምነት የሚፈፀም ጋብቻ /ዛታግሩ/፤ ድንገተኛ ጋብቻ/ራራግሩ/፣ የጠለፋ ጋብቻ /ቦአገሩ/ ፣ ተጋቢዎች ስምምነት የሚፈፀም ጋብቻ / ሹኖ ግሩ/ በመባል ይታወቃሉ፡፡'ዛታግሩ" ሁለቱ ተጋቢዎች ሣይተወዋቁ በወላጆቻቸው መልካም ፈቃድ ወይም ስምምነት ብቻ የሚጋቡበት የጋብቻ አይነት ነው፡፡ "ራራግሩ˚ ደግሞ ሣይታሰብ በድንገት የሚፈፀም የጋብቻ አይነት ሲሆን ልጅቱም ሆነች የልጅቷ ወላጆች ስለጋብቻው አንዳች እውቀት ሣይኖራቸው ወይም ሣይሰሙ አግቢው ጐረምሣ ከቤቱ ደግሶ ፈረሱን ጭኖና አጃቢ አስከትሎ ሽማግሌ ይዞ በድንገት የልጅቷ ወላጆች ቤት ሄዶ ደጅ በመገኘት የሚፈፀም የጋብቻ አይነት ነዉ፡፡ እንዲህ አይነቱ ጋብቻ ተቀባይነት ባያገኝም እንኳን የሚከፈለው የጥሎሽ መጠን ከተለመደው መጠን ከፍ ይላል፡፡
ዞካግሩ" በሶስተኛ ወገን አገናኝነት በሁለቱ ጥንዶች መካከል የሚፈፀም የጋብቻ ዓይነት ነው፡፡
አብዛኛውን ጊዜ የማግባባቱ ተግባር የሚከናወነው በሴቶች አማካይነት ሲሆን አግባቢዋም ይህንን የምታደርገው ከአግቢው የገንዘብ ወይም የሌላ ነገር ጥቅም ለማግኘት ስትል እንደሆነ ይነገራል፡፡ ጥቅማ ጥቅሙን ለማግኘት ስትልም ወንዱ ለከጀላት ሴት የተለያዩ የማግባቢያ ስልቶችን ተጠቅማ ጋብቻ እንድትፈጽም ታደርጋታለች፡፡ ይህ አይነቱ ጋብቻ በአብዛኛው ተፈፃሚ የሚሆነው በተለያዩ ምክንያቶች ባሎቻቻውን ፈትተው ወይም በሞት ተነጥቀው በተቀመጡ ሴቶች ላይሲሆን አልፎ አልፎ ባላገቡ ሴቶች ላይም ተፈጻሚ የሚሆንበት አጋጣሚ እንዳለ የብሔረሰቡ ተወላጆች ይናገራሉ፡፡ “ሹኖ ግሩ" ደግሞ በሁለቱ ተጋቢዎች ስምምነት የሚፈጸም ጋብቻ ሲሆን ሁለቱ ወጣቶች ከወላጆቻቸው እውቅና ውጭ በድብቅ ፍቅርይጀምራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ እያሉ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሣይጋቡ ልጅቷ ከፀነስች ሁለቱም ጥንዶች አንድ ላይ መኖር የሚጀምሩበት የጋብቻ አይነት ነው፡፡ ከላይከተጠቀሱት የጋብቻ ዓይነቶች መካከል ከተወሰኑት በስተቀር አብዛኞቹ በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ ሲደረጉ አይስተዋልም።በብሔረሰቡ የጋብቻ እድሜ የሴት ልጅ 18 ዓመት ሲሆን የወንድ ልጅ ደግሞ 20 ዓመት ነው፡፡ በብሄረሰቡ ዘንድ የሴት ልጅ ግርዛት የተወገዘ ነዉ፡፡
ባህላዊ የቤት አሰራር
ብሔረሰቡ ክብ ቅርጽ ያለው ባህላዊ ቤታቸው በልዩ ጥበብ አስበው ይሰሩታል። የጥድ እንጨት ለግድግዳ እና ለምስሶ ሲጠቀሙ ሐረግና የእንስት ገመድ ደግሞ ለማሰሪያነት ይጠቀማሉ፡፡ ቤቱ ተስርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ በሰንበሌጥ ወይም በስንደዶ ተከድኖ ግድግዳው በጭቃ ይመረጋል፡፡ ቤቱ ከተሸጐረ ከባለቤቱ ውጪ ማንም የብሔረሰቡ አባላት ሁለት ቤት የሚሰሩ ሲሆን አልፎ አልፎ ሶስት ቤት የሚሰሩ የብሔረሰቡ አባላት እንዳሉም ይነገራል፡፡ አንደኛው የቤተሰብ መኖሪያ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለእንግዶች ማረፊያ የሚያገለግል ነው፡፡ ሶስተኛው ካለ ለከብቶች ማደሪያነት ይጠ›ቀሙበታል።
ባህላዊ ምግብ
ቆጮ የየም ብሔረሰብ ዋነኛ ባህላዊ ምግብ ነው፡፡ ከእንስት ውጤት ብቻ ከስምንት በላይ ባህላዊ ምግቦችን በማዘጋጀት ይጠቀማሉ፡፡ የሞች እንስትን ለምግብነት ብቻ ማይሆን ለመድሐኒትነትም ጭምር እንደሚጠቀሙበት ይነገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከተለያዩ የእሀል አይነቶች እና ከጓሮ አትክልቶች የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችን አዘጋጅቶ የመመገብ ልምድ አላቸው፡፡ "ዋቶ" እና "ባራሲኛ" ከእንሰት ውጤቶች "ኤቶቱሻ" ደግሞ ከእህል ከሚዘጋጁ ባህላዊ ምግቦች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
ባህላዊ አለባበስ
የየም ብሔረሰብ የራሱ የሆነ አለባበስ አሉት፡፡የሞች ጥጥ አምርተው ፈትለው የተለያዩ አልባሳትን በማዘጋጀት ይለብሱ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከአቡጀዲ የተዘጋጀ ጥብቆ ለሕፃናት እና ለወጣቶች ኩታ ፣ ሽንሽን፡ ባለ ቀይ ጥለት የፈትል ቀሚስ እና ጃኖ ደግሞ ለሴቶች እንዲሁም ተነፋነፍ ሱሪ ፣ እጀ ጠባብ እና ነጭ ጋቢና ቡሉኮ ለአዛውንቶች ባህላዊ ልብስ በመሆን ያገለግሉ እንደነበር የብሔረሰቡ አዛውንቶች ይገልፃሉ፡፡
የለቅሶ ሥርዓት
በየም ብሔረሰብ አንድ ሰው ሲሞት የለቅሶ ስርዓቱ እንደ ሟቹ እድሜ እና ማህበራዊ ደረጃ ይለያያል፡፡ ሕፃናት እና ወጣቶች ሲሞቱ አልቅሶ ከመቅበር ውጪ የተለየ የለቅሶ ስርዓት አይከናወንም፡፡ አዋቂ ወንድ የሞተ እንደሆነ የለቅሶ ስርዓቱ ለየት ይላል፡፡ ልክ ነብሱ ከስጋው እንደተለየች የሟቹ ቤት የውጫዊ ጣራው ቡልኮ እንዲለብስ ይደረጋል፡፡ ከዚያም ወንዶች የአጋዘን ቀንድ፣ ጦርና ጋሻ በመያዝ ሴቶች ደግሞ ድብኝት እና የቦርዴ መያዣ/ ጉዶ/ ከመሬት ጋር በማጋጨት ሟች በሕይወት ዘመነ ያከናወናቸውን በጐ ተግባራት በመጥቀስ በመዝለልና በማዜም ያለቅሳሉ፡፡ ለከፈን ከተዘጋጀው ቡልኮ ጥለቱ ተቆርጦ የሟች ሴት ልጆች እና ሚስት እንዲለብሱት ይደረጋል።ቀደም ባሉ ዘመናት “ታቶሃንጉስ ሲሞት የብሔረሰቡ አባል የሆነ አዋቂ ሰው ሁሉ ፀጉሩን በመላጨት እና ፊቱን ጭቃ በመቀባት ሐዘኑን ይገልጽ እንደነበር ይነገራል፡፡ የንጉስ አስከሬን በመጀመሪያ በምርጥ ጨርቅ ይከፈንና የላም ቆዳ ይደረብበታል፡፡ የቀብር ሥርዓቱ የሚፈጸመው የተተኪው ንጉሥ ሥርዓተ ንግስና ከተከናወነ በኋላ ነው፡፡