ሀዲያ
የሀዲያ ዞን አጠቃላይ ገጽታ
የሀድያ ዞን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ውስጥ ከሚገኙ 7 ዞኖች አንዱ ሲሆን የዞኑ ቆዳ ስፋት 3,950.20 ካሬ ኪ.ሜትር ነው፡፡ ዞኑ በ13 ወረዳዎች፣7 ከተማ አስተዳደር፣ በ246 የገጠር ቀበሌዎችና 88 የከተማ ቀበሌያት የተደራጀ ነው፡፡ ዞኑን በሰሜን ጉራጌ ዞን፤ በሰሜን ምስራቅ ስልጤ ዞን በምስራቅ ሀላባ ዞን፣ በሰሜን ምዕራብ የም ዞን፣ በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና ደቡብና ደቡብ ምስራቅ ካምባታ ዞን ያወስኑታል፡፡ የዞኑ አቀማመጥ ሜዳ የበዛበት ኘላቶማ ሆኖ በተለይ በሥራ ሥር፣ በበቆሎ፣ በስንዴ፣ በእንስትና በጤፍ እንዲሁም በቀንድ ከብት እርባታ የታወቀ ነው። የዞኑ ርዕሰ ከተማ ሆሣዕና የክልሉ የአስተዳደር እና ፖለቲካ መቀመጫ ከተማ ነች፡፡ በ1999 ዓ/ም የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት መሠረት የዞኑ አጠቃላይ የሕዝቡ ብዛት 2,098,494 ሲሆን ፕላን እና ልማት ቢሮ 2017 ዓ.ም ፕሮጄክሽን ወንድ1,044,283 ሴት 1,054,211 ድምር 2,098,494 እንደሚሆን ይገመታል፡፡
በሀዲያ ዞን በርካታ ተፈጥሮአዊና ስው ሠራሽ መስህቦች ይገኛሉ፡፡ ከተፈጥሮአዊ መስህቦች፣/መካከል ፍል ውኃዎች /የሀዎራ ጠበል/ ፏፏቴዎች የገሙና፣የጎንቦራ፣ የሀብቾ፣የብላቴ/ሐይቅ/፣ ቦዬ ሐይቅ ሠንሠለታማ ተራሮች/ሽንቆላ፣ ቱላካላለም/ እና ተፈጥሮአዊ ገጽታዎች ለአብነት ሲጠቀሱ ከስው ሠራሽ መስህቦች ታሪካዊነት ያላቸው ዋሻዎች /በንዳልቾ ኡልዳ፣ ባቴና ከራራ፤ሲቢያ ጋጋኖ/ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት /የጊቤ፤የመስመስ ቅ/ገብርኤል/ ባህላዊና የወግ ዕቃዎች የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ ሆነው የውጭ አገር ዜጎች ጭምር እየጎበኙአቸው ይገኛሉ፡፡
የሀዲያ ብሔረሰብ
የሀዲያ ብሔረሰብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ የብሔረሰቡ መጠሪያ/ስያሜ/ ከአረብኛ ቋንቋ የተወሰደ ቃል እንደሆነና የቃሉም ቀጥተኛ ትርጉም “ስጦታ” ማለት እንደሆነ አንዳንድ የትውፊት መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ብሔረስቡ በዋነኛነት በሀድያ ዞን በሚገኙ 13 ወረዳዎች እና 7 ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ የሚኖር ሲሆን ከዞኑ ውጪ ደግሞ በወላይታ፣ በሲራሮ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በአጆ፣ በወንጂ፣ በመተሀራ፣ በስልጤ፣ በቀቤና፣ በማረቆ፣ በሀላባ፣ በሲዳማ፣ በየም፣ በሐረሪ፣ በአፋር፣ በኮፌሌና በካምባታ፣ዞን ጠንባሮ ልዩ ወረዳ በብዛት እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ የአማራ፣ የከምባታ፣ የጉራጌ፣ የወላይታ፣ የሥልጤና የሌሎች ብሔረሰቦች አባላትም ከብሔረሰቡ ጋር በስብጥር ይኖራሉ፡፡ የብሔረሰቡ አባላት በዋነኛነት የሚኖሩባቸው አሥሩ ወረዳዎች ሜዳማ፣ ተደፋትና ወጣገባ የመሬት አቀማመጥ ሲኖራቸው የአየርንብረቱም ደጋ፣ ወይናደጋና ቆላማ ነው፡፡ የብሔረሰቡ ዋነኛ መተዳደሪያ እርሻ ሲሆን ከብት እርባታና ንግድ በተጓዳኝ በማከናወን ኑሮውን ይመራል፡፡ ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ማሽላ፣ እንስትና በርበሬ በብሔረሰቡ አባላት ዘንድ ለፍጆታና ለሽያጭየሚመረቱ የምርት ዓይነቶች ናቸው፡፡ በብሔረሰቡ የበርካታ ከብት ባለቤት መሆን ማህበራዊ ከበሬታን ያስጥ ስለነበር ከአንድ መቶ እስከ አንድ ሺህ የማስቆጠር ወይም የማስመረቅ ስርዓት ይከናወናል፡፡
ቋንቋ
የደጋማው ምስራቃዊ ኩሽ የቋንቋ ቤተሰብ የሆነው "ሀዲይሳ" የሀድያ ብሔረሰብ አፍ መፍቻ ቋንቋ ነው፡፡ኩታገጠም በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ የብሔረሰቡ አባላት ደግሞከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ ከምባትሣ ፣ ኦሮምሚፋና ስልጢኛ በሁለተኛ ቋንቋነት ይናገራሉ፡፡ በተመሣሣይ ሁኔታ የብሔረሰቡ አባላትም ደግሞ ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ ከምባትሣ፣ ኦሮምኛንና ስልጢኛ በሁለተኛ ቋንቋነት ይናገራሉ፡፡ ሀዲይሳ አንግግር ቋንቋነት አልፎ የጽሁፍ ቋንቋ መሆን የጀመረው በ192ዐዎቹ ዓለም አቀፍ የእንግሊዝኛ መጽሀፍ ቅዱስ ማህበር መጽሐፍ ቅዱስን በሐድይኛ ቋንቋ አስተርጉሞ ካሳተመበት ወቅት ጀምሮ እንደሆነ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሌላ በኩል ከ1967-68 ዓ/ም በነበረው የእድገት በህብረት ዘመቻ ወቅት የሳባን ፊደላት በመጠቀም ለመሰረተ ትምህርት ማስተማሪያነት መዋል እንደጀመረ ይነገራል፡፡ በሀዲያ ብሔረሰብ ባህል ታሪክ እና ቋንቋ ላይ የተጠኑ ዉስን ጥናቶች ያሉ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ በዞኑ ባህል ቱሪዝም እና መንግስት ኮሚንኬሽን መምሪያ የተጠኑ በ2002 ዓ.ም የሀዲያ ባህልና ታሪክ ጥናት፣ የሀዲያ ባህላዊ ምግብ አዘገጃጀት፤ሀዲይሳ እንግሊዝኛ መዝገበ-ቃላት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከ1983 ዓ/ም ወዲህ ግን በሀገሪቱ የአንደኛ ደረጀ ትምህርትን በአፍ መፍቻ ቋንቋ የማስተማር ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ክመስከረም 1986 ዓ/ም ጀምሮ በሀድይኛ የአንደኛ ደረጃ የመጀመሪያ ሳይክል /1-4/ ሁሉም የትምህርት ዓይነቶች እየተሰጡ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሀድያ ዞን የስራ ቋንቋ ሀዲይሳ ሲሆን የፌዴራልና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሥራ ቋንቋ የሆነው አማርኛም በዞኑ በስፋት አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡
ታሪካዊ አመጣጥና አሰፋፈር የሀዲያ ብሔረሰብን ቅድመ ታሪክ አስመልክቶ በብሔረሰቡ ምሁራንና በሀገር ሽማግሌዎች የተለያዩ ሀሳቦች ይንፀባረቃሉ፡፡ ከእነዚህ ሀሳቦች ውስጥ አንደኛው የሀድያ ብሔረስብ ከእስያ ክፍለ አህጉር ተነስቶ ቀይ ባህርን አቋርጦ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል የሚለው ነው፡፡
በዚህ ገለፃ መሠረት ሀዲያዎች ከአረቢያ ፈልሰው ቀይ ባህርን በማቋረጥ በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ሐረር ላይ በመስፈር፣ ቀስ በቀስም ለእርሻ ተስማሚ የሆነ ለም መሬት እና ለከብቶቻቸው ውኃና የግጦሽ ሣር ፍለጋ በመንቀሳቀስ ባሌንና አርሲን አቋርጠው አሁን የሠፈሩበት አካባቢ እንደከተሙ ይታመናል፡፡ ይህን መሠል ረዥምና ውጣ ውረድ የሞላበትን ጉዞ በሚያደርጉበት ወቅት ጥቂት የማይባሉ የብሔረሰቡ አባላት በባሌ፣ በአርሲና በሌሎችም አካባቢዎች ተቆርጠው የቀሩና በአሁኑ ወቅት የኦሮምፋና የሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች ቢሆኑም በዘር ሀረጋቸው ግን ሀዲያ መሆናቸው ይነገራል ።
ስለ ብሔረሰቡ ታሪካዊ አመጣጥና አስፋፈር የሚያትተው ሁለተኛው አመለካከት ደግሞ፤ ሀድያን ከአረቢያና ከኤስያ ጋር በማዛመድ ከትውፊት /አፈ-ታሪክ/ የዘለቀ የታሪክ መረጃ እንደሌለው በመግለፅ ሀድያ ጥንታዊና ነባር ህዝብ (indigenous) መሆኑን በአፅንኦት ከገለፀ በኋላ የመጀመሪያውን አመለካከት በከፊል በመጋራት የብሔረሰቡ ጥንታዊና ታሪካዊ መነሻ ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ እንደሆነና ከሰፈረበት በሐረር በተለያዩ ሰብዓዊና ተፈጥሮአዊ ክስተቶች ሳቢያ ወደ ባሌ አርሲና ሌሎች አካባቢዎች በመጓዝ አሁን የሰፈረበትን አካባቢ እንደያዘ ይገልፃል፡፡
የታሪክ ምሁር ኘሮፌሰር ላጲሶ ጌድሌቦ፣ ሁለተኛውን አመለካከት የሚጋሩ ሲሆን በ1991 ዓ.ም "የሀዲያ ሕዝብና መንግስት ታሪካዊ መነሻና ሚና በደቡብ ኢትዮጵያ" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ በገፅ 29 ላይ “በደቡብ ኢትዮጵያ በምሥራቅ ከዋቤ ወንዝ፣ በምዕራብ ከጊቤ ወንዝ፣ ድረስ በሚገኘው ምድር በ15ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ የሀዲያ ሥልጣኔ /እስላማዊ መንግስት/ በአሥር ገራዶች የተከፋፈለ አሥር የአካባቢ መስተዳድሮች ወይም ክፍለ ግዛቶች የተከፋፈለ አንድ ታላቅ ጥንታዊ ሕዝብ እንደነበር' ይገልፃሉ፡፡
ስለ ሀድያ እስላማዊ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ ተጠቅሶ የምናገኘው በ14ኛው ክ/ዘመን በንጉሥ አምደ ፅዮን ዘመነ መንግስት ነው፡፡ ንጉሥ አምደዕዮን /1314-1344/ ሀድያን በ1316 በወረራ ካስገበረ በኋላ ወታደር ሲመለምልበት ቆይቷል፡፡ ይሁንና ሀዲያ በንጉሥ አምደፀዮን ቢሸነፍም ለነፃነቱና ለማንነቱ እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ማድረጉ ይታወቃል፡፡በመሆኑም “የሰለሞናዊው" ክርስቲያን ነገሥታት የሀድያ መሪዎችን አመጽ ለማለዘብና ለመግታት በማሰብ ፖለቲካዊ ተልዕኮ ያላቸው ጋብቻዎችን ከሀድያ ገራዶች ቤተሰብ ጋር በመፈፀም ጥንቃቄ የተሞላበት ግንኙነት ሲያደርጉ ቆይቷል፡፡ ለአብነትም በወቅቱ ገናና ከነበረው ንጉሥ ዘርዓያዕቆብ /1434-1486/ ኋላ ላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ህይወት ውስጥ ታላቅ ሚና ለመጫወት የበቃችውን የሀድያውን ገራድ መሐመድ ልጅ “ዛላን” ወይም እሌኒን /የንግስና ስሟ/ አግብቷል፡፡
በልጁና በአልጋ ወራሹ በበዕደ ማሪያም /1468-78/ እና የልጅ ልጁ በነበረው በልብነ ድንግል /1508-40/ ዘመንም ይኸው ፖለቲካዊ ጋብቻ ሲካሄድ የቆየ ቢሆንም ሀድያ ለነፃነቱና ለክብሩ ሲፈጽም የነበረውን ተጋድሎ ሊገታው እንዳልቻለ የታሪክ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ባህላዊ አስተዳዳር
ሀዲያ ብሔረሰብ ውስጥ አሥራ ሰባት ማህበራዊ ቡድኖች ወይም ጎሣዎች ይገኛሉ፡፡ እነርሱም ሌሞ /ኡቤኤ፣ ጋሞ፤ ላሞራ፣ ሞቾሶ፤ ዶጌኤ/ ሶሮ ወይም ቦያሞ /ሀዴ፣ሀባሮ፤ሻካህ፣ ቦሻሀ፣ ሻሼ፣ ኡሩሶ/፣ ዶዳ፣ ሶሌቾ /ባርጋጌኤ፤ ሀበሎ፤ ሀይባ፣ ባዶጎ፤ሆጄኤ፣ ዋየቦ፣ ሀንቃላ፣ አጋር-ጋሣ /ሎካ፣ዱባሞ፣ መስመስ፣ ካውካ/፣ ገንዛ፣ ኤራራ፣ መሳዋ፣ ባዳዎቾ፣ ደዋ-ዲጋላ ናቸው፡፡ እነዚህ ጎሣዎች የተለያየ ባህላዊ የአስተዳደር እርከኖችና መሪዎች ያላቸው ሲሆን፤ ይህም ከዝቅተኛው ወደ ከፍተኛው እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡
የባህላዊ የአስተዳደር እርከን
1. ምኔ /ቤተሰብ/፤ሲሆን የደረጃው /የእርከኑ መሪ/ ምኒዳና /የቤተሰብ መሪ
2. ሞሎኑ /ጎጥ/፣ ሞኦሊዳና /የጎጥ መሪ
3. ሱላአ /ነገድ/ ሱኡሊዳና /የነገድ መሪ
4. ጊዕቾ /ጐሣ/ ግዕች ዳና /የጎሣ መሪ/
5. ግራ /ብሔረሰብ/ ግዕሊዳና /የብሔረሰቡ መሪ/
የሀዲያ ባህላዊ አስተዳዳሪዎች አመራረጥ መመዘኛው ግላዊ ብቃትና የህብረተሰብ ሚዛን ናቸው፡፡ በግላዊ ብቃቱ የብሔረሰቡን ባህላዊ እሴቶች ጠንቅቆ የማወቅ፣ እንደበተ ርቱዕነት፤ አስተዋይነት፣ ቀናነት፣ ቸርነት፣ ይቅርባይነት፣ ሀብት እና ወዘተ... ናቸው፡፡ ከማህበረሰብ ሚዛን ደግሞ ከጐሣ ወይም ከቤተሰብ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአስተዳደር ልምድ፣ የቤተሰብ ወይም የጐሣ ደረጃ ከፍ ያለ መሆን፣ የሚነቀፍበት እንከን ወይም ጉድለት የሌለው መሆን ናቸው፡፡ ከእነዚህ መስፈርቶች አንፃር፤ ለኃላፊነት የታጨው ግለሰብ፣ በግል ብቃቱና በህብረተሰቡ መመዘኛዎች ተመዝኖ ብቁ ሆኖ ሲገኝ እንደሚሾምበት የሥልጣን እርከንና ደረጃ መጠነኛ /ጨምበለቃ ሉባ/ ወይም ከፍ ያለ /ጨለለቃ ሉባ/ ድግስ ተደግሶና ተመርቆ ለኃላፊነት እንዲበቃ ይደረጋል።
በብሔረሰቡ ባህላዊ አስተዳደር የዳኝነት ሥልጣን የየጎሣው መሪዎች ነው፡፡ ዳኝነት የሚካሄደው በተሰየመ ሥፍራ ወይም ችሎት ሲሆን፤ የዚህ ባህላዊ ችሎት /Hata/መሪ “ወሸባ” ይባላል፡፡ ባላባታዊ የአገዛዝ ሥርዓት ወደ ሀድያ የገባው በ19ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ አፄ ምኒልክ ሀድያን በጦርነት ካሸነፉ በኋላ ባደረጉት የሹመት አሰጣጥ ሥርዓት የቀድሞው ብሔረሰቡ ባህላዊ አስተዳደር መሪዎች ባላባት ይሁኑ በማለታቸው ከነባሩ ባህላዊ አስተዳደር ልምድና ችሎታ ያላቸውን መርጠው በሾሙበት ወቅት እንደነበር ይነገራል፡፡ የሀድያ ባህላዊ አስተዳደር የተለያዩ የሥልጣን ደረጃዎች አሉት፡፡ እነርሱም "አድላ” /ገራዲ/፣ "ወሽባ" "ዳዳቾ"፣ “አስማቼኤ”፣ “አበጋዝ”፣ “አባጋዳ”፣ “አንጃንቾ"፣ ግደብ ገራድ'! “አሽን ገራዳ፣ “ወለብ ገራዳ”፣ “ሀጋኢ ገራዳ”፣ “ይማም” እና "መጋባ" የተሰኙ የማዕረግ መጠሪያ አላቸው፡፡ ከላይከተዘረዘሩት ውስጥ አድል /ገራዳ/ ከፍተኛው የሥልጣን ደረጃ /እርከን/ ሲሆን፤ ለብሔረሰቡ ነገሥታት /ሡልጣኔት/ የሚስጥ የማዕረግ መጠሪያ ነው፡፡
አድላ (Adil) ከሚል የአረብኛ ቃል የተወረሰ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የብሔረሰቡ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት “ሴራ" በመባል ይታወቃል፡፡ ዋንኛ ተግባሩም ባህላዊና ማህበራዊ ህግጋትንና ሥርዓትን ማስከበር፣ ህዝቡን ከጥቃት መከላከልና ማደራጀት፣ በአጎራባች ጐሣዎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ማስወገድና የአስተዳደሩን ሹማምንት መስየም ናቸው ፡፡ የባህላዊ አስተዳደሩ ሥርዓት /ሴራ/ ዳኝነት (Hafa) ከሚያተኩርባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ የግድያ፣ የቤት ቃጠሎ፣ የጠለፋ፣ የስርቆት፣ የክህደት፣ የድንበር ማለፍ /ማፍረስ/ ወንጀሎች ዋንኛዎቹ ናቸው፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ሳቢያ በደል ቢፈፀም ተበዳይ ጉዳዩን ለዳኞች ያመለክታል፡፡ ዳኞቹም ፍትሐዊ ብያኔን ለመስጠት የተለያዩ ባህላዊ የመረጃ አሰባሰብ ስልቶችን የሚጠቀሙ ቢሆንም ዋንኛው ግን ቃለ መሐላ /ሒድሮ/ ነው፡፡ በዚህ ስልት ተጠርጣሪው አላየሁም “ዓይኔ ይታወር" አልሰማሁም “ጆሮዬ ይደፈን" በማለት እንዲምል ይደረጋል:: መሀላውን የፈራ እውነቱን ገልጦ ያወጣል፡፡ ሌላው ስልት “ጥቁር ማስወጋት" (hee mach cha amaddissima) ይባላል፡፡ በዚህ የምርመራው ስልት ተጠርጣሪው ግለሰብ፤ “አላየሁም አልሰማሁም እኔም ሆንኩ ዘርማንዘሬ የተረገመ ይሁን" በማለት ይምላል፡፡ ሦስተኛው የምርመራ ስልት ደግሞ የሰውና የተለያዩ ቁሣቁሶችን የአሻራ መረጃዎችን በማሰባሰብና በማስመስከር የሚከናወን ነው፡፡ ይህ ስልት(Naqaasha) ተብሎ ይጠራል፡፡ የቅጣት ዓይነቶቹም እንደ ወንጀሉ ዓይነት ይለያያሉ፡፡ ለአብነትም የበደለ ተበዳዩን ዝቅ ብሎ ይቅርታ እንዲጠይቅ ማስደረግ (ussiisimma)፣ የበዳይን ንብረት ማውደም (Butta) ከጥፋቱ የማይመለስ አመፀኛን ከጐረቤትና ከዘመድ እንዲገለል ማድረግ (Yayyimma) ናቸው፡፡ ሌላው የቅጣት ተበዳይን እንዲክስ ማስደረግ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት (guzumo'o) ይባላል፡፡ በብሔረሰቡ ባህላዊ አስተዳደር እስካሁን ባለው ልምድ የሴቶች ሚና እጅግ አናሳ ነው። በመሆኑም ሴቶች በብሔረሰቡ ታሪክ በዳኝነት ሥርዓት ውስጥ ተመርጠው ወይም ተወክለው አያውቁም፡፣ ሆኖም ግን በደል በደረሰባቸው ጊዜ በደላቸውን የማሣወቅና አቤቱታቸውን የማቅረብ ባህላዊ መብት አላቸው።
ለአብነትም ማንኛውም ወንድ ሚስቱን ያለ አግባብ ቢበድላት የፆታ አጋሮቿ፣ ከየመንደሩ ተጠራርተው በመውጣት በግራ እጃቸው በትር እየጎተቱ በደሉን ባደረሰባት ሰው ደጅ በመሰብሰብ በሚስቱ ላይ እየፈፀመ ያለውን በደል እንዲያቆም ያሳስባሉ፣ ያስጠነቅቃሉ፡፡ ይህ ሴቶች የፆታ አጋራቸውን በደል ለመቃወም የሚያደርጉት ሠልፍ “ኡሉሉ'' ወይም “ሙጉአ" በመባል ይታወቃል፡፡
ባህላዊ ዕሴቶች
የጋብቻ ሥርዓት
ሀዲያ በኢትዮጵያ የመካከለኛው ዘመን ታሪክ /127ዐ- 1855/ ከደጋማው ክርስቲያናዊ መንግሥት ይልቅ እንደ ይፋት፣ አዳል፣ ሐረር፣ ባሌ፣ ደዋሮ እና ፈጠጋር ከመሳሰሉት እስላማዊ መንግስታት ጋር በነበረው የንግድ ትስስርና ቁርኝት ሳቢያ የእስልምናን ሐይማኖት እንደተቀበለ የታሪክ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይሁንና ሀዲያ ከእስልምና ሐይማኖት ጋር በብዙ መልኩ የሚቀራረብ “ፈንዳኖ” የተሰኘ ባህላዊ እምነት እንደነበረው የሚገልፁ ትውፊቶች አሉ፡፡ ይህ ነባርና ጥንታዊው ፋንዳኖ ባህላዊ እምነት በእስልምና በመለወጡ እንደከሰመ በብሔረስቡ ይታመናል፡፡ አዛውንቶች በሀዲያ ብሔረሰብ የተለያዩ የጋብቻ ዓይነቶች አሉ፡፡ እነርሱም /ጤአቃንቻ/በተጋቢዎች ወላጆች ስምምነትና በጎ ፍቃድ ጥሎሽ ተጥሎና የቃል ማሠሪያ ሥርዓት ተፈጽሞ የሚመሠረት ጋብቻ /ጎሳኖ/ ወንዱ የፈለጋትን ሴት ሳያማክርና የእርሷንም ሆነ የቤተሰቦቿን መልካም ፍቃድ ሳይጠይቅ በኃይልና በማስገደድ የሚፈፀም የጠለፋ ጋብቻ፣ /ሄራንቻ/ በተጋቢዎች በጎ ፍቃድ ያለማንም ጣልቃ ገብነትና ያለሠርግ የሚፈጸም ጋብቻ /ለጎ/ ባል ሲሞት የባል ወንድም ወይም የቅርብ ዘመድ የሟችን ሚስት የሚያገባበት የውርስ ጋብቻ እና /እልገንማ/ የልጅቷ ወላጆችና ቤተሰብ ያለልጅቷ ፍቃድ ከወንዱ ጋር በሚያደርጉት ስምምነት የሚፈፀም ጋብቻዎች ናቸው፡፡ በብሔረሰቡ ባህል የሴት ልጅ የጋብቻ ዕድሜ ከ18 ዓመት በላይ ሲሆን የወንድ ልጅየጋብቻ ዕድሜ ደግሞ ከ2ዐ ዓመት በላይ ነው፡፡ በጥንት ዘመን የብሔረሰቡ ኢኮኖሚ በአብዛኛው ከከብት ርቢ ጋር የተሣሠረ ስለነበር ከከብቱ ብዛትና ከሚሰማሩበት ቦታ ስፋት አንፃር በአንዲት ሚስት ብቻ ይህን ሁሉ ሀብት መቆጣጠርና ማሠማራት አይቻልም፤ የቤተሰብ ብዛትም ከጠላት የሚስነዘርን ጥቃት ለመመከት ጠቃሚ ነው በሚል በብሔረሰቡ ዘንድ ከአንድ በላይ ጋብቻ በአዎንታዊ ገፅታው ይታይ እንደነበርይነገራል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ሚስቶች በርካታ ልጆችን መውለድ ድህነትን፣ ጉስቁልናን፤ የመሬት ጥበትን ከተለያዩ ሚስቶች በሚወለዱ ልጆች መካከል መቀናናትን መቃቃርንና ጥላቻን የሚፈጥር በመሆኑ፤ እያደር እየቀነሰና እየቀረ በመሄድ ላይ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ጥሎሽ ለመስጠት የሚገደደው ወንዱ ሲሆን፤ የጥሎሽ ዓይነቱም በጥሬ ገንዘብና በዓይነት የሚሰጥ ነው፡፡ የጥሎሽ መጠኑ በአማካይ ከብር 2000-7000 እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ በዓይነት የሚሰጡት በአብዛኛው የተለያዩ አልባሳት ሲሆኑ በጥንት ዘመን ደግሞ ማርቴሬዛ፣ የቀንድ ከብትና ቡሉኮ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ብሔረሰቡ የተለያዩ የሠርግ የአፈጻጸም ሥርዓቶች አሉት፡፡ እነርሱም ኪፋ (Kiffa) ከአንድ መቶ በላይ ሠርገኛ የሚታደምበትና ለሁለት ቀናት ውለው አድረው የሚስተናገዱበት፣ እጅግ ከፍ ያለ ድግሥ /ጨለለቃ/ የሚደገስበት እና አህያ፣ ፈረስና በቅሎ ከነሙሉ ዕቃቸው እንዲሁም የቀንድ ከብቶችና የተለያዩ ስጦታዎች ለልጅቷ ቤተሰቦች የሚበረከትበት ኢልሞቻ (Illmocha)፣ በልጅቷ ቤተሰብ ለአንድ ቀን ውለው የሚያድሩበት ከ70-100 የሚደርሱ ሠርገኞች የሚስተናገዱበት የሠርግ ዓይነት ሲሆን የስጦታው መጠንና አይነት ከኪፋ አንፃር አነስ ያለ ነው፡፡ አንጋቻ (Angacha) ከ5ዐ-6ዐ ሠርገኞች የሚታደሙበትና ለአንድ ቀን አድረው የሚስተናገዱበት ነገር ግን መለስተኛና ያልተጋነነ ስጦታ የሚበረከትበት ሲሆን፤ ሆሻሮ (Hoosharoo) ደግሞ የደርሶ መልስ ሠርግ ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት ሙሽራው ወደ ሙሽሪት ቤት ከሠርገኞች ጋር አይሄድም፡፡ በመሆኑም ሙሽራዋን ወደ ሙሽራው የሚያመጧት የሙሽራው ሠርገኞች ናቸው፡፡
በብሔረሰቡ ባህል ሴት ልጅ ስትወልድ በቤተሰቦቿ ዘንድ ደስታና ዕልልታ ይሆናል፡፡ የደስታውና የዕልልታው መጠን ግን በፆታው ዓይነት የሚወሰን ነው፡፡ ወንድ ልጅ ሲወለድ ለ6 ጊዜ እልል ሲባል ሴት ከሆነች እልልታው ወደ ሦስት ጊዜ ይወርዳል፡፡ ይህም የብሄረሰቡ ወግ ለወንድ ፆታ የላቀ ክብር እንደሚሰጥ አመላካች እንደሆነ ይታመናል፡፡
በሀድያ ባህል ለአራስ ሴት የሚደርግላት እንክብካቤ ክፍተኛ ነው፡፡ ሀድያወች አራሷን ቪጂራ” በመባል የሚታወቀውን የብሔረሰቡ የዕደ ጥበብ ውጤት የሆነ አልጋ ማረፊያ ይሆናት ዘንድ በመስራትና በማዘጋጀት የፍየልና የበግ ጠቦት አር ው ደሙን አቅቤ ጋር ቀላቅለው በማጠጣት ከሁለት እስከ ሦስት ወር ይቀልቧታል: ምልክት እንዲሆናትም ለእንገቷ ጌጥ /ቀናፋ/ ይታሠርላታል፡፡ ይህም ሥርዓት ራኄ ኢሻ ይባላል።
የቤት አሠራር
ብሔረስቡ ሁለት ዓይነት የተለያዩ የቤት አሠራሮች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ከላይእስከታች ሣር የሚለበስ ጐጆ ሲሆን፤ “ሁጉማኦ" ይባላል ሁለተኛው ግድግዳውና ጣሪያው ተለይቶ ጣሪያው በሣር የሚከደንና “ፌንጋሞ" በመባል የሚጠራ ነው። በቤት አሠራሩ ሂደት ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊዎች ወንዶች ሲሆኑ በምርጊቱ ላይየሚሳተፉት ግን ሴቶች ናቸው፡፡
ባህላዊ የምግብ አዘገጃጀት
የሀዲያ ብሔረሰብ ከ45 በላይ ባህላዊ ምግቦችና የተለያዩ ባህላዊ መጠጦች እንዳሉት ይነገራል፡፡ ብሔረስቡ በየዕለቱ ከሚመገባቸው የዘውትር ምግቦች መካከል ቆጮ፣ ቂጣ፣ ወተት እና የወተት ተዋፅኦ፣ ቆሎ፣ ቡና ድንችና "ቡሎ" ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ነጭሽንኩርት /ቱማ/ እና ጤና አዳም /ቀንተለማ/ ከምግብነት በተጨማሪ ለባህላዊ መድኀኒትነት ሲያገለግሉ የኮሶ ዛፍን ለመድሐኒትነት ይጠቀማሉ፡፡
ባህላዊ አለባበስ
በብሔረሰቡ ባህላዊ የአለባበስ ሥርዓት ውስጥ ብዙውን ጊዜ ልጆች የበግ ለምድ /ለበሳ/ የጨርቅ ጥብቆና ቁምጣ፣ ወጣቶች የበግ ለምድና ጥብቆ፣ ሴቶች ከቆዳ የሚሠሩ አምባ /ቆጦጣ፣ ለጣ ቂጣ/ እና ከጨርቅ የሚሠሩ የተለያዩ አልባሳት ይለብሳሉ፡፡ አዛውንቶች ጎሌ፣ ፎንሣ፣ ስንጣፋ፣ ቀምቢሳ ቡቡኮ ደበሼ ሲለብሱ የባህላዊ አስተዳደር መሪዎችና ጀግኖች ካባ፣ ጃኖ፣ ሰሬዋና፣ ሰንጠፋ/ሱሪ/ወዘተ በመልበስ ከላይ ባርኔጣ ይደፋሉ፡፡ ወዘተ
ሲለብሱ የባህላዊ አስተዳደር መሪዎችና ጀግኖች ካባ፣ ጃኖ፣ ሰሬዋና፣ ሰንጠፋ/ሱሪ/ወዘተ በመልበስ ከላይ ባርኔጣ ይደፋሉ፡፡ ወዘተ
ባህላዊ ጨዋታ
በተለያየ ፆታና የዕድሜ ክልል የሚገኙ የብሔረሰቡ አባላት ሐዘንና ደስታቸውን የሚገልፁባቸው የተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች አሏቸው። ለአብነትም ህቦ፤ ዎሮዮ ዎሮዮ፤ ኡዋዮ፣ ቦያሴሌሜ እና ሆዩሜ በብሔረሰቡ ኮረዶችና ኮበሌዎች ይዜማሉ፡፡ ያገቡ ሴቶችና ወንዶች ዋር ይጫወታሉ። በሥራ ወቅት ማሌሌ ሃሌል ግምሆሌ፣ ሆዩሜ ሆዩሜ" ለማነቃቂያነት ይቀነቀናሉ፡፡
ሻሮ ድራንቻ”፣ ለፉከራ “ድራንቻ" ደግሞ ለሙገሣ የሚዜሙ ናቸው፡፡ እነዚህን ጨዋታዎች ሲያቀነቅኑ የሚጠቀሙባቸው ባህላዊ መሣሪያዎች ክራር/ዴታ/፣ ዋሽንት /ጋምባቢያ/፣ ከበሮ /ጦርቤ/ እና ጥሩንባ /ጡሩንቡላ/ ናቸው፡፡
የለቅሶና ሀዘን ሥርዓት
በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኝ የብሔረሰቡ አባል በሞት ሲለይ ይለቀሣል፣ ይታዘናል፡፡ ይሁን እንጂ የቀብሩ እና የለቅሶው ሥርዓት ይለያያል፡፡ ጀግኖች፣ መሪዎች፣ ገራዶች፣ አድላዎች እንዲሁም በመልካም ስም የሚታወቁ አዛውንቶች ሲሞቱ ቤተሰብና የቅርብ ቤተዘመድ በሚስጥር የቀብር ሥርዓቱን ይፈጽማሉ፡፡
ከዚያም ለሣምንት ወይም ለ15 ቀን አልፎ አልፎም ለ30 ቀናት ለለቅሶው ሥርዓ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጐ ሲያበቃ ከ8-16 የሚደርሱ ፈረሰኞች አረዃኖ በአራቱም ማዕዘን ሁለት ሁለት ሆነው እየዞሩ የሚቹን ስምና የዘር ሀረ7) እየጠቀሱና እየቆጠሩ በሕይወት በነበረበት ወቅት የፊፀማቸውን ጀብድና ገድል እያነሱ በማወደስ ለቅርብም ሆነ ለሩቅ ዘመድ እከሌ ሞቷል ኤባሪ ዶየኮ/ በማለት የሟቹን ሞት ያረዳሉ፡፡ መርዶውን የስሙ ለቀስተኞችም ባህላዊ አልባሳትን በመልበስ የተለያዩ የጦር ዕቃዎችን በመታጠቅና በመያዝ የቅርብ ዝምድና ያላቸው ደግሞ እህል በበቅሉ በመጫን ወደ ለቅሶው ሥፍራ ይጐርፋሉ። የማቹ ደጅ ሰፊ ከሆነ በደጁ ላይካልሆነም ወደ ሰፊ ሜዳ በመውጣት ለአውራ፣ ለገራዳ፣ ለአድላ፣ ለጀግና "ሆሌማንቾና ናጋራታ ህማማ" የተሰኘ ባህላዊ የለቅሶ ጭፈራ ይጨፈራል፡፡ ነጋሪት ይጎስማል፡፡ በሆላማንቾ የጭፈራ ሥርዓት የሟች ሚስት ካባ ትለብሳለች፤ ልጆቹና የቅርብ ዘመዶቹ ለምድ /ሱምሌንድ/ ለብሰው የአንበሳ ጎፈር ደፍተው፣ ጦርና ጋሻ ይዘው ደግነቱን፣ አስተዋይነቱንና ጀግንነቱን እያወደሱ ያለቅሱለታል፡፡ ሟቹ ገዳይከሆነ በገደለው ቁጥር ሸምበቆ ተተክሎ እየተቆጠረ ይለቀሳል፡፡ ሚስቱ የነብር ለምድ /የሁማንትቾና የአንሾክቾ/ ለብሣ የአእዋፍ ላባዎችን በፀጉሯ ሰክታ ታለቅሳለች፡፡