Skip to main content

ከምባታ

                                           የከምባታ ዞን አጠቃላይ ገጽታ
ከምባታ ዞን በክልሉ ካሉ ዞኖች አንዱ ሆኖ በ7 ወረዳዎች፣ በ6 በተማ አስተዳደር፣ በ97 የገጠርና በ28 የከተማ ቀበሌያት የተደራጀ ነው፡፡ ዞኑ ሰሜንና በሰሜን ምዕራብ ከሀድያ ዞን፣ በምዕራብ ከዳውሮ ዞን፣ በሰሜን ምስራቅ ከሀላባ ዞን በደቡብ ከዎላይታ ዞንና በምስራቅ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር ይዋሰናል። የመሬቱ አቀማመጥ በአብዛኛው ወጣ ገባነት ያለው ኘላተማና ለሁሉም ዓይነት ግብርና ሥራ ተስማሚ ነው። የዞኑ ቆዳ ስፋት 1,253,80 ካሬ ሜትር ሲሆን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ   ፕላን እና ልማት ቢሮ 2017 ዓ.ም ፕሮጄክሽን መሠረት የዞን ህዝብ ብዛት ወንድ 489,405 ሴት 496,360  በድምሩ 985,765 ነው።
የዞኑ ዋና ከተማ ዱራሜ ከተማ ስሆን የዱራሜ ከተማ 2016ዓ.ም ጀምራ የማዕከላዊ ኢትዮጵያዊ ክልል መንግስት  የግብርና እና ገጠር ልማት ክላስተር ዋና መቀመጫ ከተማ ነች፡፡ዞኑ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦች ያሉት ሲሆን ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል በአንገጫ ወረዳ የሚገኘው ዳዋ ዋሻ፣ ሀምበርቾ ተራራ ላይ የሚገኘው ሀምበርቾ 777 ደረጃዎች  ፣መሳላ ዘመን መለወጫ፣የአጆራ ፏፏቴ ትክል ድንጋይ፣ሶሶ ፏፏቴ፣ትጋ ዋሻ፣ቅድስት አርሴማ የፈዉስ ፀበል ተጠቃሾች ናቸው፡፡
                                  የከምባታ ብሔረሰብ
የከምባታ ብሔረሰብ በክልሉ ካሉ ብሔረሰቦች አንዱ ሲሆን በዋናነት የሚገኘው በከምባታ ዞን በሚገኙ  ወረዳዎችና ከተማ አስተዳዳሮች እና በዱራሜ ከተማ አስተዳደር ሲሆን ከዞኑ ውጪ በተለያዩ ቦታዎች ማለትም በክልሉ በሀዲያና፣ በወላይታ፣ በጉራጌ፣ በስልጤ፣ በዳውሮ፣ በካፋ፣ በሀላባ፣ በሀዋሣ፣ በሻሸመኔ፤ በአዲስ አበባ፣ በወሊሶ፣ በጂማ፣ በመተሀራ እና በወንጂ፣ ጋምቤላ ፣  በብዛት ይገኛል፡፡
የከምባታ ብሔረሰብ ስያሜ ወይንም ትክክለኛ የቃሉ መጠሪያ ታሪካዊ አመጣጥና ትርጉም አስጣጥ ሁለት ተቀራራቢ የሆኑ አስተያየቶች በተለያዩ ወገኖች ይሠጣሉ፡፡ የመጀመሪያው ወገን "ከምባታ” የሚለው ቃል ስያሜ የተገኘው ከምባት" ከሚለው የከምባትኛ ቃል ሲሆን፤ የቃሉ ትርጉም "እዚህ ነው" ማለት እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች የሚያቀርቡት ማስረጃ ጥንት የብሔረሰቡ አባላት በተለያየ ምክንያት ከሌሎች ጋር ለሚያደርጉት ጦርነት ለመገናኘት እና ለመሰባሰብ የሚወስነ-በት ቦታ “ከምባት" እየተባለ እንደሚነገር ያስረዳሉ፡፡ ሁለተኛው ወገን ደግሞ “ከምባታ” የሚለው ቃል “ከምባት'' ከሚለው የብሔረሰቡ ቋንቋ እንደተገኘ እና የቃሉ ትርጉምም “ይህ የምንኖርበት ሥፍራ ነው፡፡ "ወይንም "የምንኖርበት ሥፍራ እዚህ ነው፡፡" ማለት እንደሆነ፣ በዚህም የተነሣ የብሔረሰቡ ቀደምት አባቶች በዚሁ ሥፍራ መኖር እንደ ጀመሩ ይገልፃሉ፡፡ በዚህም መሠረት "ከምባታ" የሚለው ቃል "ከምባት" ከሚለው የከምባትኛ ቃል ተወስዶ የብሔረስቡ ስም እና የብሔረሰቡ መኖሪያ ቦታ ስያሜ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። የከምባታ ብሔረሰብ ዛሬ ሠፍሮ በሚገኝበት ሥፍራ ሌሎች የሀዲያ፣ዶንጋ ፣ የአማራ፣ የጉራጌ፣ የጠምባሮና የዎላይታ ብሔረሰቦች በከተማና በገጠር አብረው ይኖራሉ፡፡
የብሔረሰቡ አባላት በዋናነት በዞኑ ውስጥ የሠፈሩባቸው አካባቢዎች መልክዐ-ምድራዊ አቀማመጥ በከፊል ሜዳማ፣ በአብዛኛው ተራራማ፣ ተዳፋትና ወጣ ገባ በመጠኑም ቢሆን ሸለቋማ ገፅታ ያለው ሲሆን የአየር ንብረቱም በሶስቱም ሥነ-ምህዳር ማለትም በደጋ፣ በወይናደጋ እና በቆላ የተከፈለ ነው፡፡ የህዝቡ ዋና መተዳደሪያና የኢኮኖሚ መሠረት ግብርና ነው፡፡ በመሆኑም የተለያዩ የሰብል ምርቶችን ከማምረት ጐን ለጐን ማካሄድና የዕደ-ጥበብ ምርቶችን ማምረት የተለመዱ ተግባሮች ናቸው፡፡
በዋናነት የሚመረቱ የሰብል ምርቶች መካክል በቆሉ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ አተር: ባቄላ፣ ተልባ፣ ጤፍ፤ ማሽላ አደንጓሬ፣ ዳጉሣ፤ እጃ፣ ምስር ለአብነት ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ በተጨማሪ በረዥም ዘመናት በምግብነትና በቤት መስሪያ አገልግሎቱ በስፋት የሚታወቀው የእንስት ተክል በሁሉም ወረዳዎች ይገኛል፡፡ በአካባቢው ከሚመረቱ የፍራፍሬና የአትክልት ዓይነቶች አቡካዶ፣ ፓፓዬ፣ ማንጐ፣ ጐመን፤ ሙዝ፤ ብርቱካን፣ ሎሚ፣ ሠላጣ፣ ቆስጣና ካሮት በስፋት ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከፍጆታ አልፈው ለማዕከለዊ ገበያ በማቅረብ በክፍተኛ ደረጃ የገቢ ምንጭ በመሆን ለማህበረሰቡ ክፍተኛ ጠቀሜታ እየሰጡ ያሉ ምርቶች ቡና፣ ልዩ ልዩ ቅመማ ቅመሞች በተለይ ዝንጅብል ትልቁን ሥፍራ ይይዛል፡፡ አብዛኛው የከምባታ በብሔረሰቡ በግብርና ሥራ የሚተዳደር ቢሆንም የተወሰኑ ክፍሎች በንግድና በእደ-ጥበብ ሙያ ተሠማርተው የዕለት ተዕለት ኑሮአቸውን ይመራሉ፡፡
በተለይ በእደ-ጥበብ የሙያ መስክ የተሠማሩ እነዚህ ክፍሎች ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ልዩ ልዩ ባህላዊ መሣሪያዎችን እና እቃዎችን በአካባቢው ከሚገኙ ልዩ ልዩ ባህላዊ ቁሣቁሶች እያመረቱ ለሕዝቡ ያቀርባሉ፡፡ ቀደም ሲልም ሆነ አሁንም ህዝቡ በስፋት ባህላዊ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን መጠቀም ባህል አለው፡፡ በዚህ የሥራ ዘርፍ የተሠማሩ የእደ ጥበብ ባለሙያዎች በብሔረሰቡ ቋንቋ “ሉባሞ" በመባል የሚጠሩ ሲሆን የቃሉ ትርጉም “የእጅ ጥበብን /ሙያን/ሥራን/ አዋቂ" እንደ ማለት ነው፡፡ በእነዚህ ክፍሎች የሚመረቱ የእደ ጥበብ ምርቶች በአብዛኛው ከብረታ ብረት፣ ከቆዳ፣ ከእንጨት ከአፈር የሚሠሩ የቤት ውስጥ መገልገያዎችና የእርሻ መሣሪያዎች ናቸው፡፡
                               ቋንቋ
የከምባታ ብሔረሰብ ቋንቋ ከምባትሳ ሲሆን ከኩሽ የቋንቋ ቤተሰብ ይመደባል፡፡ የከምባትሳ ቋንቋ ከጠምባርኛ፣ ከሀላቢሳ፤ ክሀዲይሳ፣ ከቀቤናኛ፣ ከሲዳምኛ ቋንቋዎች ጋርም ተቀራራቢነትና ተመሣሣይነት ያለው ሲሆን የብሔረሰቡ አባላት ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ በአቅራቢያቸው የሚገኙ አጎራባች ብሔረሰቦችን በተለይበድንበር አካባቢ የሚነገሩ ቋንቋዎችን ማለትም ሀዲይኛን፣ ዎላይትኛን፤ ጠምባርኛን‐ እንዲሁም በብዙዎች ዘንድ አማርኛ እንደሁለተኛ ቋንቋ ይጠቀማሉ፡፡
የከምባትኛ ቋንቋ ከንግግር ቋንቋነት አልፎ የጽሑፍ ቋንቋ ለመሆን የበቃ ነው፡፡ ከ1985 ዓ/ም በፊት ለጎልማሶች የመሠረተ ትምህርት መስጫ ቋንቋ በመሆን አገልግሏል፡፡ እንዲሁም የተለያዩ የማስተማሪያ መፅሐፍት ከ1985 ዓ/ም ጀምሮ የተለያዮ ማስተማሪያ መጽሐፍት ታትመዋል። ቀደም ሲል ቋንቋው የጽሑፍ አገልግሎት ሥራ ላይ ይውል የነበረው የሣባ ፊደል በቋንቋው ሰዋሰዋዊ አገባብና እገላለፅ የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ ባለመሆኑ የተነሣ እንዲቀርና ተወስኖ በምትኩ የላቲን ፊደል አገልግሎት ላይ እንዲውል ተደርጐ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ከ1987 ዓ/ም ጀምሮ ቋንቋው /የላቲን ፊደል ገበታን በመጠቀም/ የአንደኛ ደረጃ የመጀመሪያ ሣይክል /ከ1ኛ-4ኛ ክፍል/ የትምህርት ቋንቋ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

ከዚህም በተጨማሪ ለአንደኛ ደረጃ ሁለተኛ ሣይክል /ከ5ኛ-8ኛ ክፍል/ እንደ አንድ የትምህርት ቋንቋ እና ከትምህርት ቋንቋነትም አልፎ በዞኑ ውስጥ በአንዳንድ መንግስታዊ ተቋማት በተለይ እንደ ፍ/ቤቶች ባሉ ሥፍራዎች የማህበረሰቡ አባላት ለክርክር ሂደትና ሀሳባቸውን ለመግለፅ እንዲችሉ በወሳኝ ዘርፎች የሥራ ቋንቋ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። በአጠቃላይ ለከምባትኛ ቋንቋ ዕድገት ከ1985 ዓ.ም ወዲህ ለቋንቋው የላቲን ፊደል ከተቀረፀለት ጀምሮ በርካታ የጽሑፍ ሥራዎች በቋንቋው ተከናውነዋል። የተለያዩ የመማሪያ መፅሐፍትን፣ በዞኑ ማስታወቂያና ባህል መምሪያ የተዘጋጀ ከምባትኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላት፤ የተለያዩ የኃይማኖት መፅሐፍት በቋንቋው የትርጉም ሥራ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ህገ መንግስት በቋንቋው መዘጋጀት ለአብነት የሚጠቀሱ በቋንቋው የተሠሩ ሥራዎች ናቸው፡፡ እንዲሁም በ2004 የብሔረሰቦች ምክር ቤት እና የዲላ ዩኒቬርሲቲ በካምባታ ጣንባሮና ዶንጋ ብሔረሰቦች የጋራ እሴች ጥናት ታትሞ ጥቅም ላይ እንዲዉል ተደርጓል።

                                  ታሪካዊ አመጣጥና አሠፋፈር
ከዞኑ ማስታወቂያና ባህል መምሪያና ከሀገር ሽማግሌዎች በተገኘ መረጃ መሰረት የከምባታ ብሔረሰብ ጥንታዊ አመጣጡ ከአንድ ከተወሰነ ቦታ በአንድ ወቅት የሆነ ማይሆን በተለያየ ጊዜ ከተለያየ ቦታ እንደመጣ ይነገራል፡፡ ቀደምት ናቸው የሚባሉት ሰባት የተለያዩ ጐሣዎች እንደሆኑና እነዚህም ኤፌጌና፣ ኤቤጄና፣ ሂኒራ፣ ጠዞ፤ ጉሮማ፣ ፉጋና ጋዴና በመባል እንደሚታወቁ እና ሁሉም በአምበርቾ ተራራ ላይይኖሩ እንደነበር የብሔረሰቡ አዛውንቶች ያስረዳሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከመካከለኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተለያዩ ጐሣዎች ከሲዳማ፣ ከአማራ፣ ከወላይታ፣ ከዳውሮ፣ ከሀዲያ፣ ከጉራጌ፣ ከኦሮሚያ... ወዘተ አካባቢዎች በተለያየ ጊዜ መጥተው በአምበርቶ ተራራ ላይ እንደሠፈሩ፤ ሁሉም ስለአመጣጣቸው የራሳቸው የሆነ የተለያየ ምክንያት እንደነበራቸው የሚነገር አፈ ታሪክ አለ፡፡
ባህላዊ አስተዳደር
የከምባታ ብሔረስብ ሲነሣ "የአምበርቾ ተራራ አብሮ ይነሣል፤ ይወደሣል፤ ሁለቱ የተቆራኙ እና የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ አምበርቾ የሚታወቀው በተራራነቱ ብቻ ሣይሆን እንደ ቅዱስ ሥፍራ የሚታይ የአምልኮ ሥርዓት የሚካሄድበትም ቦታ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ቦታው ጥንት የከምባታ መሪዎች ወይንም ነገሥታት መኖሪያ ሥፍራ ሆኖ እንደሚያገለግል ይነገራል፡፡
“አምበርቾ ተራራ ስያሜውን ያገኘው በድሮ ዘመን ተራራው ላይ ይኖር የነበረ አንድ የከምባታ ንጉስ ከህዝቡ በግብር መልክ ለንጉሱ የተዳረች ልጃገረድ በእጅዋ ላይአምባር ተደርጐላት ሲትኖር የንጉስ ቤት ኑሮ ተመችቷት እየወፈረች፣ ሲትመጣ በእጅዋ ላይ የተደረገው አምባር እጅዋን ያቆስለዋል ከዚያን ንጉስ የልጅቱን እጅ መቁሰል አይቶ “ምን ሆነሽ ነው?" ብሎ ሲጠይቃት እሷም “አምባር እቾ" ብላ ስለመለሰችለት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተራራው “አምበርቾ” እየተባለ መጠራት ተጀመረ። በብሔረሰቡ ቋንቋ “አምባርቾ” ማለት “አምባሩ በላኝ" እንደማለት ነው፡፡ የአምባታ ጐሣዎች በአምበርቾ ተራራ መስፈር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ "የአምበርቾ "ተራራ ዋና የአምልኮ ቦታ ሆኖ ቆይቷል፡፡
የከምባታ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ ባህላዊ አስተዳደር የነበረው ሲሆን በዚህ የአስተዳደርሥርዓት ሁሉም የብሔረሰቡ ጐሣዎች በአንድነት መክረውና ዘክረው በስምምነት ይኖሩ ነበር፡፡ የባህላዊ አስተዳደሩ የበላይ አካል ሥልጣን “ንጉስ” /ወማ/ ነው፡፡ ንጉሱ የሚስየመውከአያት ጐሣ ሆኖ በልጅ እየተተካ የሚቀጥል ነው፡፡ በብሔረሰቡ ይህ ባህላዊ ሥርዓት ከወማ/ንጉስ/ አኖ እስከ ወማ ድልበቶ ድረስ እንደቆየ በአፈ ታሪክይነገራል፡፡ ሁሉም የብሔረሰቡ ጐሣዎች የሚወከሉበት ይህ ባህላዊ አስተዳደር "ምክርቤት" /ፓርላማ/ “ጎጎታ"በመባል ይታወቃል፡፡ እነዚህ የጐጐታ መሪዎች የሚመረጡት ከጐሣ መሪዎች ነው፡፡ የጎጎታ አስተዳደር በብሔረሰቡ የሚፈጠሩ ከበድ ያሉ ወንጀሎችን ወይንም ግጭቶችን ይፈታሉ፤ ብሔረሰቡን ከጠላት ለመከላከል እንዲቻል የጦር ሠራዊትን የመመልመል ተግባርን ያከናውናል፡፡
የባህላዊ አስተዳደሩ የሥልጣን እርከን /ደረጃ/ ከጠቅላላ ብሔረስቡ /ወረድ/ ብሎ በጎሣ ደረጃም ተግባራዊ ይደረግ ነበር፡፡ በጎሣ ደረጃ አቅም ያለውና ንብረት ያለው፣ ታዋቂና ጠንካራ አቋም ያለው ሰው ጎሣውን ሊመራና ሊያስተዳድር ይችላል ተብሎ ስለሚታመን እንዲህ አይነቱ ሰው የየጐሣው ባህላዊ መሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ሰው /የጎሣ መሪ በብሔረሰቡ ቋንቋ በተወሰነ አካባቢ ያሉትን የጎሣ አባላትን የሚመራ /የሚያስተዳድር/ “ቦኪ ዳና” የሚባል ሲሆን በቤተሰብ ደረጃ ያለው ታላቅሚኒ ባህሩ” ተብሎ ይጠራል፡፡ እነዚህ በየእርከኑ ያሉ “ዳናዎች”፣ “ቦኪዳ ናዎች ! እና ሚኒ ባህሮች" በየደረጃው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ይፈታሉ፣ የተጣሉትን ሰዎች ያስታርቃሉ፤ የበደሉት እንዲክሱ ያደርጋሉ፡፡

ቀደም ሲል የነበረው የከምባታ ብሔረሰብ ባላዊ አስተዳደር ሠጄ ጎቾ የሚባል የሥልጣን እርከን ነበረው። የዚህ የሥልጣን እርክን /መዋቅር/ ታሪካዊ አመሠራረት ከንጉስ/ ከወማ ድልበቶ ጋር የተቆራኘ ነበር። ከከምባታ ወማዎች አንዱ የነበሩት ድልበቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብር ያስጀመሩትና ስለ ግብሩ ዓይነትና አቀራረብ ደንብ ያወጡት የከምባታ ህዝብ ቤተ መንግስትና ቤተ መቅደስ በመባል በሚታወቀው በ "ሀምበርቾ ተራራ ላይ ነበር። ቀደም ሲል የነበሩት ወማዎች የየራሳቸው የሆነ አስተዳደራዊ ደንቦች ቢኖሯቸውም የመሻሻልና የዕድገት ለውጥ የተደረገው በወማ ድልበቶ የስልጣን ዘመን እንደነበር ይነገራል። የወማ ድልበቶ አስተዳደር ዘመን ከአጐራባች ብሔረሰቦች በነበረው ግጭት ጠላት በሁሉም አቅጣጫዎች የከምባታን ህዝብ ለመውጋትና ድንበሩን ለመግፋት ከፍተኛ ዝግጅት ያደርግ የነበረበት ዘመን ነበር። በዚህ የተነሣ የመጣውን ጠላት ለመመከትና ለመቋቋም፤ ህዝቡንም ከጥቃት ለመላከል የሚያስችል አቅም ለመገንበት፣ የስንቅና የግብር አቀራረብን ለማመቻቸት የከምባታን ክልል በ3ዐ የአስተዳደር /የአገዛዝም/ ክፍሎች ከፋፍለው አዋቅረዋል። ከዚህም በኋላ እነዚህን የአስተዳደር አካባቢዎችን “ሠጄ" ጎቾ" በማለት እንደሰየሟቸውና ለሁሉም የአስተዳደር አካባቢዎች “ጎቺ ዳና ካታ'' በኋላም "ሠንጋ ቆሮ" በመባል የሚታወቁ ተጠሪዎችን መሾማቸውን የብሔረሰቡ የዕድሜ ባለፀጋዎች ይናገራሉ፡፡
የከምባታ ብሔረሰብ የራስ የሆነ የግጭት አፈታት እና የሽምግልና ዳኝነት ሥርዓት አለው፡፡ በብሔረሰቡ ዘንድ ብዙውን ጊዜ ግጭቶች የሚከሰቱት ከጠለፋ፣ ከውርስ ንብረት፣ ከመሬት፣ ከውርስ ጋብቻና ከሌብነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ነው፡፡ በእነዚህና በሌሎች ሣቢያ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ብሔረሰቡ የሚፈታበት፣ የተለያዩ ስልቶች አሉት፡፡ አንዳንድ ቀለል ያሉ አለመግባባቶች ሲከስቱ በቤተሰብ ወይም በሠፈር ደረጃ በሽማግሌዎች ድርድር ያልቃሉ፡፡ ነገር ግን ከበድ ያሉ ግጭቶች እንደ ዘረፋ፣ ሰው ግድያ፣ ድንበር ነክ፣ የጠልፋ ጋብቻ የሚፈቱት በብሔረሰቡ ከፍተኛ ባህላዊ አስተዳደር ነው፡፡ አደገኛ የሆኑና አስከፊ ውጤት ሊያስከትሉ የሚችሉ ግጭቶችን ለማስወገድ ብሔረሰቡ “ጉድን ገምበልን" የሚባል ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት አለው፡፡ ይህ ሥርዓት ተግባራዊ የሚደረገው በተለይ የነፍስ ግድያ ወንጀል ሲፈፀም ነው፡፡ የገዳዩንና የሟችን ቤተሰብ ለማስታረቅ ጥቁር በግ በማረድ ሁለቱም ቤተስቦች ደሙን እንዲረግጡት ተደርጐ እርቁ ይፈፀማል፡፡ ከእርቁ በኋላ ሁለቱም ወገኖችዳግም ላለመጋጨት መሀላ ይፈፅማሉ። በጠለፋ ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶች ለመፍታት ጠላፊው በሴቷ ቤተሰቦች በራፍ ላይ በሬ በማሰር በሽምግልና ድርድሩ እንዲያልቅ ይደረጋል፡፡ ከዚያም ጉዳዩ ሁለቱም ወገኖች በሚመርጧቸው ሽማግሌዎች ይታያል፡፡
በባህሉና በወጉ መሠረት እልባት ያገኛል፡፡ ዘረፋና ሌብነትን የመሣሠሉ ጉዳዮች በአውጫጭኝ ሥነ-ሥርዓት ይፈፀማሉ፡፡ በብሔረሰቡ በባህላዊ ሥርዓት መሠረት አልታረቅም የሚል ከማህበረሰቡ ይገለላል፡፡ ቤተሰቦቹ ከሌሎች ቤተሰቦች፣ ከብቱ ከሌሎች ከብቶች ጋር እንዳይገናኝ፤ በማንኛውም ማህበራዊ ህይወት እንዲገለል ማህበራዊ ማዕቀብ ይጣልበታል፡፡ የዚያኑ ያህል ጥፋተኞችንና ወንጀለኞችን በማህበረሰቡ ደንብና ሥርዓት መሠረት ካሣ እንዲከፍሉ ይደረጋሉ፡፡ የከምባታ ብሔረሰብ ባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት ሴቶችን በውሣኔ ሰጪነት አያሣትፍም። በመሆኑም የወንድ የበላይነት በብዛት የሚንፀባረቅበት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ባህላዊ ሥርዓቱ ክንውን ወቅት በተለይ በእርግማንና በምርቃት ሴቶች ተሣታፊ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ብሔረሰቡ አደገኛ /ከረር/ ያሉ ግጭቶች ሲከሠቱ ጉዳዩን ለማርገብ ሴቶች ልብሣቸውን /ነጠላቸውን/ አንጥፈው ከለመነ ፀቡ ይረግባል፡፡ እነዚህን ሴቶች ረግጠው አልፈው የሚጣሉ እንኳን ቢኖሩ “በጎጎታ” ደንብ መሠረት ከፍተኛ መቀጮ ይጣልባቸዋል፡፡ ስለዚህ ሴቶች ምንም እንኳን በባህላዊ አስተዳደሩ ውስጥ ተሣትፎ ባይኖራቸውም በባህሉ በጣም ይከበራሉ፤ ተሰሚነትም አላቸው፡፡
                                          ባህላዊ እሴቶች
                                         የጋብቻ ሥርዓት
የከምባታን ብሔረሰብ የማንነት አሻራ ከሚያንፀባርቁ ባህላዊ እሴቶች መካከል አንዱ ባህላዊ የጋብቻ ሥርዓቱ ነው፡፡ በብሔረሰቡ የተለመዱ ባህላዊ የጋብቻ ዓይነቶች አራት ሲሆኑ እነዚህም የመፈቃቀድ ጋብቻ ፣ ቆርሲሻ” አባብሎ የማግባት፣ “ሔረቱታ” ፣የጠለፋ ጋብቻ እና “ምዱሃ” ፣ የውርስ ጋብቻ “ረግታ" በመባል ይታወቃሉ፡፡ የመጀመሪያውና “ቆርሲሻ የሚባለው ባህላዊ ጋብቻ በቤተሰብ ስምምነትና መፈቃቀድ የሚመሠረት የጋብቻ ዓይነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጋብቻ በአራት የተለያየ መልኩ የሚፈፀም ሲሆን እነዚህም በብሔረሰቡ ቋንቋ ኪፋ”፣ “አልሞ"፣ “ቁቦዋቻ“ እና “አንሼንአሡሃ" በመባል ይታወቃሉ፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት መካከል “ኪፋ” እና “ኢልሞ” ተመሣሣይ የአፈፅፀም ሥነ-ሥርዓት አላቸው፡፡ በነዚህ የጋብቻ ዓይነቶች በጣም ሀብታም የሆነና ከፍተኛ ሀብት ንብረት ያለው ቤተሰብ ለዝና እና ለእውቀት ተብሎ በክፍተኛ ወጪ ሠርግ ተደግሶ የሚፈፀም ነው።
ይሁን እንጂ “የኪፋ" የሠርግ ድግስ ከ ኢልሞቻ - የሠርግ ድግስ ይበልጣል። በኪፋ የተዳረች ሴት በብሔረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ክብር አላት:: በዚህ የሠርግ ሥርዓት የወንዱ ሙሽራ አጃቢዎች ባህላዊ ጨዋታቸውን እየተጫወቱና እየጨፈሩ በሙሽሪት ቤተሰብ ዘንድ ለአዳር ይሄዳሉ፡፡ እዚያው እየበሉና እየጠጡ አድረው በማግስቱ ከሙሽሪት ቤተሰብ ጥሩ ጥሩ ስጦታዎች ተበርክቶለት የሚከናወን ነው፡፡ በዚህ የጋብቻ ዓይነት ለአጃቢነት ወደ ሙሽሪት ቤት የሚላክ ሰው በጥንካሬው የተመረጠ ይሆናል፡፡
ተጋቢዎቹም ከሙሽሪት ቤተሰብ ፈረስና በቅሎ ከነሙሉ እቃዎቹ፣ የከብት ስጦታ (ጌጌያ ወይፈን፤ጊደር፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የቤት ቁሳቁሶችን በተሟላ ሁኔታ ይሸለማሉ፡፡ ይህ የጋብቻ ዓይነት በጣም የተከበረና ህጋዊ በመሆኑ በብሔረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ወንዱ ለወደፊት ኑሮው ትሆነኛለች ብሎ የሚፈልጋትን ልጅ ለወላጆቹ ይገልፃል፡፡ ወላጆቹም ከልጃቸው ጓደኞች ጋር በመሆን ወደ ልጅቱ ቤተሰቦች ዘንድ በመሄድ "ገድ™ ወይም ሚልኪ በብሔረሰቡ ቋንቋ “ጭዕቹ” እንዲያጠኑ ይደረጋል፡፡ ሚልኪው ወይንም ገዱ ጥሩ ነው ወይንም ልጅቷን እንዲያገባ “ጭዕቾ” ፈቅዶአል የሚባለው ለቅኝት ወደልጅቱ ቤተሰብ የተላኩ ሰዎች ልጅቱን ቤት ካገኝዋት፣ቡና ወይንም ምግብ እየተሠራ ወይም እየተበላ ከደረሱ ገዱ መልካም ጥሩ/ እንደሆነ ይታመናል፡፡


ይህን የገጠማቸውን ክስተት የተላኩት ሰዎች ለወንዱ ቤተሰብ ከገለፁ በኋላ ቀጣዩ ተግባርለሴቷ ቤተሰብ “ልጃችሁን ለልጃችን" የሚል ጥያቄ ይቀርባል። ከዚህ በኋላ በሁለቱ ወገኖች ሽማግሌዎች ነፃ የውይይት ጊዜ እና ቦታ (ሀሌቾ) ይወስናል፡፡ በዚህ ዕለት በሚደረገው ውይይት የሴቷ ወላጆች እጅ የሚሳምበት በብሔረሰቡ ቋንቋ “የአንጋ ሰንቃ” ሥርዓት የሚካሄድበት ቀነ ቀጠሮ ይወሰናል። የዚህ ባህላዊ ሥርዓት የሚከናወንበትም ሆነ የጥሎሽ መስጫ የሚፈፀምበት ቀናት ማክሰኞ ሐሙስ፣ቅዳሜና እሁድ ናቸው፡፡ የወንዱ ቤተሰብ ሽማግሌዎች ቀደም ሲል በተያዘው ቀጠሮ መሠረት “የአንጋ ሱንቃ” ወይንም እጀ መሣሚያ ስጦታ ይዘው በዕለቱ በሴቷ ቤተሰብ ቤት ይገኛሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ የጥሎሽ ቀን ይወሰናል፤ በተወሰነው ቀን መሠረት ጥሎሽ ይጣላል፡፡ ከወንዱ ቤተሰቦች ለሴቷ ቤተሰቦች የሚሰጠው የጥሎሽ መጠን እንደየቤተሰቡ አቅም የተለያየ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ማር፣ ቡልኮ፣ የአባትና የእናት ልብስ፣ ሣር በብሔረሰቡ ቋንቋ “ሐሩፋ” አይቀሬ ናቸው። ለልጅቱ የሚሰጠው ልዩ ልዩ ጌጣ ጌጥ የልብስ ጥራትና ለጥሎሽ የሚሰጠው የገንዘብ መጠን እንደ ወንዱ ቤተሰብ አቅም ይለያያል፡፡ ይህ የጥሎሽ ሥርዓት በሚካሄድበት ሰዓት በልጅቱ ቤተሰብ መጠነኛ ግብዣ ለእንግዶች ይዘጋጃል። በዚህ ዕለት የሠርጉ ቀን በሁለቱ ወገኖች ስምምነት መሠረት ይወሰናል፡፡ የሠርጉ ዕለት የወንዱ ሙሽራ ሚዜዎችና የተወሰኑ የቤተሰቡ ሽማግሌዎች ወደ ሙሽሪት ቤተሰብ ቤት ሲገቡ ሌሎች አጃቢዎች ውጪ እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ የሙሽሪት ቤተሰቦች የሙሽሪትን የስጦታ እቃዎች ቆጥረው ካበቁ በኋላ ሙሽሪትን ለሚዜዎችና ለሽማግሌዎች ያስረክባሉ፡፡ የተረከቡት ሚዜዎች ሙሽሪትን መጀመሪያ በፈረስ ላይ ከዚያም በበቅሎ ላይ አስቀምጠው ጉዞ ወደ ወንዱ ቤት ይጀመራል። ባዝራ ላይየሚያስቀምጡበት ምክንያት ባዝራ በተፈጥሮዋ ወላድ ስለሆነች ሙሽሪትንም ውለጂ ክበጂ እንደማለት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሙሽራው ቤተሰብ ቤት እንደደረሱ በቤቱ ደጅ ላይ ሣርባለበት ኬሻ “ኤንዴ ቤሮ” ተነጥፎ ሙሽሪትን ያስቀምጣሉ፣ ወንድና ሴት ህፃናትን በሁለቱ ታፋዎቿ ላይ አስቀምጠው “ወንድና ሴት፣ ልጅ ውለጂ" እያሉ እናቶች መልካም ምኞታቸውን ይገልፃሉ፤ በእግርዋ ጣቶች ላይም ትኩስ ወተት ያፈሣሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተፈፀመ በኋላ ሙሽሪት ወደ ቤት ስትገባ የሙሽራው እህት ሙሽራዋ ወደ ቤት እንዳትገባ በሩን ትይዛለች፡፡ የዚህም ምክንያት ወንድሟ ትዳር ሲይዝ ለእህቱ የሚኖረው ፍቅርእንደሚያንስ ያመለክታል የሚል ባህላዊ እምነት አለ፡፡ ይሁን እንጂ ለሙሽራው እህት የተወሰነ ገንዘብ ተሰጥቶ በሩን እንድትለቅ ይደረጋል።
"ክቆርሲሻ" የጋብቻ ዓይነት አንዱ አጥቦ መስጠት አንሸን ቆርሲሷ የሚባለው ሲሆን ይህ የጋብቻ ዓይነት ህጋዊ የሆነ ጋብቻ ሆኖ ያለድግስ በሙሽራው ቤት ብቻ ተደግሶ የሚፈፀም የጋብቻ ዓይነት ነው፡፡ በዚህ ጋብቻ ዓይነት ሙሽራው ከሠርገኞቹ ጋር አብሮ አይሄድም፤ እንደ ሽልማት የሚሰጥ ስጦታም አይኖርም፡፡ በዚህ የሠርግ ሥርዓት በሀብት እጥረትም ሆነ በሌላ ምክንያት ጥሎሽ ሣይስጥ ምንም አልፈልግም "ልጅህን ለልጄ አጥበህ ስጥ" በማለት የሚፈፀም ነው፡፡ ሁለተኛው የጋብቻ ዓይነት “ሔረቱታ” ወይንም የማባበል ጋብቻ በመባል የሚታወቅ ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ ጋብቻ ከቤተሰብ ፈቃድና እውቅና ውጪ ባህላዊ ሥርዓቱን የመጠበቅ በሁለቱ ተጋቢዎች ስምምነትና መፈቃቀድ ብቻ የሚፈፀም ነው፡፡ ይህ ጋብቻ በአብዛኛው የሚከሰተው የቤተሰብ ተቃውሞ ሲገጥም፣ ለሠርግ ድግስ አቅም ሲያጥር፣ለጥሎሽ የሚሆን ገንዘብ ሲታጣ ነው፡፡
የዚህ ዓይነት ጋብቻ ከተፈፀመ ከሶስት ቀን በኋላ የወንዱ ቤተሰቦች ወደ ልጅቱ ቤተሰቦች ሽማግሌ ልከው ልጃችሁ እኛ ዘንድ ስላለች አትፈልጓት በማለት መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ለየትኛውም የጋብቻ ዓይነት አፈፃፀም የሚላክ ሽማግሌ ለሁለቱም ወገኖች ቀረቤታ ያለው ፤ በባህላዊ ሽምግልናው ሥርዓት በቂ አቅም አለው ተብሎ የሚታመን ሰው መሆን አለበት፡፡ በሔረቱታ ለተፈፀመ ጋብቻ ሽምግልና ተካሂዶ እርቅ ከወረደ በኋላ የወንዱ ቤተሰብ ኮርማና ማር (ወርጁሙሃ፣መለቡሃ) ይዘው ለጥፋታቸው ይቅርታ ይጠይቃሉ፡፡ በዚህ መልኩ ከተግባቡ በኋላ የወንዱ ቤተሰብ ጥሎሽ ያመጣሉ፤ በመጨረሻም ጋብቻው ባህላዊ እውቅና ያገኛል፡፡
ሶስተኛው የጋብቻ ዓይነት በብሔረሰቡ ቋንቋ “ሞዱ ሃ” በመባል የሚታወቀው የጠለፋ ጋብቻ ሊሆን ጋብቻው ከሴቷም ሆነ ከቤተሰቦችዋ ዕውቅና ወይም ፍላጐት ውጪ በወንዱ አስገዳጅነት ብቻ በጉልበት የሚፈፀም ህገ ወጥ ጋብቻ ነው። ወንዱ ለጋብቻ የሚፈልጋትን የፈለጋትን ሴት ያጠናል፣ ከጥናቱ በኋላ የጋብቻ ጥያቄውን ለሴቷ አቅርቦ ከእርሷ ፈቃደኝነቱ ሲጠፋ የግድ ማግባት አለብኝ በሚል ስሜት ጓደኞቹን አስተባብሮ አሣቻ ቦታ በመጠበቅ ልጅቱን ይዘው ይሄዳሉ፡፡ በባህሉ የጠላፊው ጓደኞች ልጅቱን የሚሸከሙት እግቢው ወይንም ጠላፊው አስቀድሞ እጅዋን ሲነካት ነው።

የጠለፋ ጋብቻ የሚፈፀመው የልጅቱ ወይንም የልጅቱ ቤተሰብ ፈቃደኝነት ሲታጣ ብቻ አይደለም፡፡ እንዳንድ ጊዜ ክጥሎሽና ከሠርግ ወጪ ለመዳን ሲባልም በሁለቱ ወገኖች ስምምነት ይፈፀማል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሴቷ ቤተሰብ ልጃቸው የወደደችውን ወንድ እንዳታገባ ተቃውሞ ካቀረቡባት ወይንም የሴቷ ወገኖች አግቢውን ወደውት እያለ ልጅቱ ግን ፈቃደኛ ሳትሆን ከቀረች ከቤተሰቦቿ ጋር በሚደረግው ምክክርና ስምምነት ወንዱ እንዲጠልፋት ይደረጋል፡፡
በቆርሲሻ ፣በ”ሔረንቻ”ም ሆነ በጠለፋ ትዳሯን የመሠረተች ሴት ልጅ ለሙሽራው ቤተሰብ የክብር እንግዳ ነች፡፡ የወንዱ ወላጆች ወንድሞቹና እህቶች ለሙሽሪት ሌላ ስም ያወጡለታል እንጂ በስምዋ አይጠሯትም፡፡ በባህሉ “ኤዜቾ” ተብላ ትጠራለች፣ ትርጉሙም “ሙሽሪት” እንደ ማለት ነው፡፡ እናትና አባት ሙሽሪትን “አንቺ' በማለት አይጠሩም፡፡ ሙሽሪት ቤቷን እስከምታሟሙቅና ሥራ እስከምትጀምር ድረስ የወንዱ እናት እንሰት እየፋቀች ከገበያም የተለያዩ እቃዎችን እየሸመተች ታቀርብላታለች፡፡ በከምባታ ባህል አንዲት ሴት ትዳር ከመሰረተች ቢያንስ እስከ ሦስት ወራት ድረስ ከቤቷ ሣትወጣ፣ በማንኛውም ማህበራዊ ጉዳይ ሳትሣተፍ፣ የቤት ውስጥ ሥራ ሳትሰራ ጫጉላ ቤት ተቀምጣ እንድትቀለብ ይደረጋል፡፡ ከጫጉላ ቤት ቆይታ በኋላ ( ከ3-1ዐ ወራት) ባለው ጊዜ የሙሽሪት አማትና የጐረቤት ሴቶች ወደ ገበያ ይዘዋት ይወጣሉ፡፡ በዚህ ሥርዓት ሙሽሪት ባህላዊ የአሸማመት ዘዴን ትለምዳለች፤ ከዚህን ቀን ጀምሮ በራስዋ ገበያ ወጥታ ትሽምታለች፣ በቤትዋ ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችንትሠራለች፤ በማህበረሰቡ ውስጥ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዩች ሁሉ መሣተፍ ትጀምራለች፡፡
አራተኛውና የመጨረሻው የጋብቻ ዓይነት “ረጊታ" /የውርስ ጋብቻ የሚባለው ሲሆን አፈፃፀሙ ባሏ በወጣትነት በጐልማሣ ዕድሜው/ ሲሞት የሟች ወንድም ወይም የቅርብ ዘመድ የሟችን ሚስት እንዲያገባ ይደረጋል። ይህም የሚሆነው የሟች ሚስት ሌላ ባዳ አግብታ ንብረት እንዳይባክን፣ ልጆች በሌላ አባት እንዳይጐሣቆሉና በአባታዊ ስሜት ወራሽ የሆነው እንዲያሳድግ ታስቦ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በብሔረሰቡ ባህል የውርስ ጋብቻ ሁለት ገፅታ ያለው ነው፡፡ አንደኛው ገፅታ ባል የሞተባት ሴት የባል ዘመድ ወይም ወገን የሆነ እንዲወርላት የማድረግ ሲሆን ሌላው ደግሞ ሚስት የሞተችበት ባል/ወንድ የሚስቱን እህት ወይንም የቅርብ ዘመድ ይወርሳል ።የዉርስ ጋብቻ ብዙውን ጊዜ በቤተሰብ ወይም በቤተዘመድ ሽማግሌ ውሣኔ መሠረት በግልጽ የሚፈፀም ሲሆን እንዳንድ ጊዜ የወራሽንም ሆነ የሚወረሰውን ስው ሙሉ ፈቃደኝነትን የሚጠይቅ ነው ፡፡
የበዓላት አከባበር
የከምባታ ብሔረስብ ከጥንት ጀምሮ ካቆያቸው በርካታ ባህላዊ እሴቶች መካከል የመሳላ የከምባዎች የዘመን መለወጫ በዓል የአከባበር ሥርዓት አንዱ ነው፡፡ በብሔረሰቡ የመሳላ በዓል አከባበር የተለየ ትርጉምና ክብር፤ ተሠጥቶት በድምቀት ይከበራል፡፡ ከዚህ የተነሣ የብሔረሰቡ አባል የሆነ ህፃን፤አዋቂ፣ ሀብታም፣ ድሃ፣ ሴት፣ ወንድ ሣይባል ሁሉም በየበኩሉ በዓሉን ለማክበርደፋ ቀና እያለ ድርሻውን ይወጣል፡፡ ይህ ባህላዊ በዓል በማህበረሰቡ ዘንድ “ማሣላ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን በዓሉ ከብቶች ከልካይ የሌለበትን የግጦሽ ሣር በግላጭ የሚያገኙበት፣ የሚደሰቱበት፤ ሀብታምና ደሀው ሁሉም እኩል ጠግበው የሚያድሩበት፣ ከቦታ ርቀት የተነሣ ተራርቆ የቆየው ዘመድ አዝማድ የሚገናኝበትና የሚጠያየቅበት፣ ህፃናት “የእንኳን አደረሳችሁ" ስጦታ የሚያበረክቱበት በዓል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የመስቀል በዓል ማሣላ እንደ ዘመን መለወጫ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት የመሸጋገሪያ ወቅት ተደርጐ ስለሚቆጠርና ይኸውም ክትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ በመሆኑ በመላው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ግምትና ቦታ የሚሰጠው ትልቅ በዓል ነው፡፡ የከምባታ ብሔረሰብ የመስቀል በዓልን ከሌሎች በዓላት ይልቅ ልዩ ክብር ስጥቶት እንዲያከብር ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ የብሔረሰቡ አባላት ዕድሜንና ዘመንን የመስቀል በዓልን በመጠቀም ስለሚቆጥሩ ነው፡፡ የአንድን ሰው እድሜ ለማወቅ ስሌት ውስጥ መግባት ሣይሆን ስንት መስቀልን እንዳሣለፈ ብቻ መጠየቅ በቂ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሌላው ምክንያት በዓሉ ሰውም ሆነ ከብት እኩል የሚጠግቡበት ወቅተ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም “ከባለቤቱ ጋር የከረመ ሆድ በመስቀል እለት ይጠግባል፡፡” የሚል አባባል በማህበረሰቡ ዘንድ መኖሩንና ይህም አባባል ምንም ይሁን ምን ያህል የተራበ እንኳን ቢሆን በመስቀል በዓል ወቅት ይጠግባል፤ጤናውን ብቻ ይስጠው፡፡” ለማለት እንደሆነ ይነገራል፡፡
በከምባታ ብሔረሰብ ዘንድ  መሳላ በዓል በድምቀት የሚያከብረው መስከረም 17 ቀን ይሁን እንጂ በርካታ ቅድመ ዝግጅቶች ከሁለት ወራት በፊት ይከናወናሉ፡፡ በዚህን ሰሞን የሁሉም ትኩረት ለበዓሉ በመሆኑና ሌሎች ተግባራት ስለማይከናወኑ ወንዶች ለከብቶች የሚሆን የግጦሽ ሣር ከልለው ያስቀምጣሉ፤ ለበዓሉ የሚሆን የማገዶ እንጨትና የእርድ አብቶችን የሚያዘጋጁ ሲሆን እናቶች ደግሞ የቆጮ ዝግጀትና የቅቤ እቁብ “ቡሪ ውጁት በመግባት ይዘጋጃሉ፡። በመስቀል በዓል ያልተገናኘ ዘመድ በሕይወት እንዳለ አይታስብም ።
ሁለተኛው የመስቀል በዓል ዝግጅት የሚከናወነው በብሔረሰቡ “ሌን የእንግጫ ቀን/በመባል በሚታወቅበት ዕለት ነው፡፡ በሌሎች ዘንድ የእንቁጣጣሽ ቀን እየተባለ የሚታወቀው መስከረም 1ቀን በብሔረሰቡ ዘንድ “ሌንጃ ባር” ወይንም “የእንግጫ ዕለት" በመባል ይጠራል፡፡ በዚህ ዕለት የሠፈሩ ህፃናት ልጆች እየጨፈሩ፣ እንግጫ ለመንቀል ወደ ወንዝ ይሄዳሉ፡፡ ከወንዝ ሲመለሡ በቡድን እየሆኑ የለቀሙትን እንግጫ ይቀማማሉ ይነጣጠቃሉ፤ ደካማውንና ሀይለኛውን ጉልበተኛውን ለመለየት ነፃ ትግልም ይገጥማሉ፡፡ ከዚህም በኋላ እየጨፈሩ የያዙትን እንግጫ ከየቤቱ እየገቡ የሽማግሌዎችን እጅ እየሳሙ ይወጣሉ፤ ወዲያውኑ ምርቃት ይቀበላሉ፡፡
ሁሉም የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ልጆቹና ሽማግሌዎቹ በአንድነት እንግጫውን በቤቱ ምሰሶ በር ያስቀምጣሉ፡፡ የእንግጫ ስጦታ የቀረበላቸው አባወራና እማወራ ለዚሁ ዕለት ተብሎ ከተዘጋጀው ባህላዊ ምግብ ያስተናግዷቸዋል፡፡ ከመስተንግዶው በኋላ ተመርቀው ወደ ቀጣዩ ቤት ይሄዳሉ፤ የደስታ መግለጫ ስጦታው፣ መስተንግዶውና በመጨረሻም ምርቃቱ በተመሣሣይ መልኩ ይከናወናል፡፡ ከዚህ ዕለት ጀምሮ በሁሉም ሰው ቤት እንግጫው በቤቱ ምሰሶ ላይ እየተገመደ ይታሠራል፡፡
                                                        ባህላዊ የቤት አሰራር
የብሔረሰቡ ባህለዊ ቤቶች አሠራር ዕደ ጥበባዊ ክህሎት የውስጥ አደረጃጀትን በሚ የሣይ መልኩ ለመሥሪያው የሚያስፈልጉ ዕቃዎንችን አሠራሩንም በዝርዝር የሚያ ሣይ መልኩ ይሆናል፡፡ የከምባታ ቤት ከመጠን ወይም ስፋት አኳያ በሰስት ደረጃ ይከፈላል። ይህውም ጋሞሚኒ፣ አልፈን ሚና እና ዘገርሚን ናቸው፡፡ “ጋሙሚኒ በጣም ሰፊና የብሔረሰቡ ትልቅ አቅም ያላቸው የሚሰሩትንና በባህላዊ ይዘቱ የተሟላ ነው። ዝገሪሚኒ እንደ ኩሺና ሆኖ "ከጋሙ” ወይም “ደርሰሚኒ” ቤት በስተኋላ የማሠራ ለምግብ ማብሰያነት የሚያገለግል ነው፡፡ “አልፍንሚኒ" ከፊት ለፊት በመጠነኛ ስፋት ተሠርቶ ለእንግዳ መቀበያነት የሚያገለግል ነው፡፡ "ደርሶ ቤት እስከ መሬት ድረስ ይወርድና አራት ሜትር የሚሆን ታዛ ብቻ ቀርቶ ይሠራል። ሶስቱም ቤቶች የሚሠሩት ከአንድ ሜትር እስከ 1:30 ሜትር ዝቅ ብሎ በመቆፈር ነው ።


                                  ባህላዊ ምግብ አዘገጃጀትና አመጋገብ
ከምባታ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ የምግብ አዘገጃጀትና አመጋገብ ሥርዓት አለው፡፡ ከጥንት ጀምሮ ከ45 የማያንሱ የምግብ ዓይነቶችና 10 የመጠጥ አይነቶች አሉት፡፡ ዋና ዋናዎቹ የምግብ አይነቶች፡
“ቀሙበታ" በማንኛውም ወቅት የሚዘጋጅ
➢ “ሙጩጩታ" ለአመት በዓል ለአራስ ጥሪ፣ ለእንግዳ ተብሎ ከአይብ ፤ ከቁርጥ ሥጋና ወተት ጋር የሚቀርብ ባህላዊ ምግብ
➢ "ቤጡታ አልፎ አልፎ ቆጮ ለቡና ቁርስ ማቅረብ ሲፈለግ እንደ ብስኩት ተጠፍጥፎ የሚዘጋጅ ነው፡፡
➢ "ሎቤታ'' ከተንቦ የበለጠ ከሙጩጮ ያነስ ዳቦ ቢጤ ወፍራም ቂጣ ነው፡፡
➢ "በሽኩታ' ቆጮ ዱቂት ተነኩሮ ከድንች፣ ከጐመንና ከአደንጓሬ ጋር ሲቀላቀል
➢ "ሙቹታ" ቡላ ልክ እንደ ቆጮ ዱቄት ተደርጐ ከተዘጋጀ በኋላ ተነኩሮና በእንስራ ተቀቅሎ የሚሰራ ሆኖ አብዛኛውን ጊዜ ለእንግዳ፣ ለወላድ ለሙሽራ እና ለሰርገኛ ክብር የሚዘጋጅ ነው፡፡
➢ ትርሹት' ክቡላ የሚሰራ ወፍራም ገንፎ
➢ "ቡላምብልታ" የተፈረፈረው የቆጮ ዱቄት ከጐመን፣ ከዱባ ፤ከድንች ጋርተቀላቅሎ የሚስሩ ናቸው ።
                                               ባህላዊ አለባበስ
የከምባታ ብሔረሰብ ባህላዊ አለባበስ የሰዎችን ማህበራዊ ቦታን መሰረት ያደረገ ነበር። ንጉሶች ወይም ወማዎች እና የጐሣ መሪዎች ጃኖ፣ በርኖስ፣ እጀጠባብ፣ ሲላንፈሎ ወይም ሱሪ ይለብሳሉ፡፡ ሌሎች መሪ ያልሆኑት ቆላ የሚባል ከቆዳ የተሰሩ እና ብርድልብስ ዓይነት ፣ፈዕለሣ ፊትና ኋላ ብቻ የሚሸፈን ሱሪ መሰል የበግ ለምድ ወንዶች ይለብሱና “ባልቶ” ወይም ትንሿ ሸማ ለለቅሶና ለገበያ ይለበሳል፡፡
በከምባታ ብሔረሰብ ባህላዊ አለባበስ በማህበራዊ ቦታ ብቻ ሣይሆን በዕድሜና በፆታ የተመሰረተ ነው፡፡ ወንዶች ልጆች የበግ ለምድ ሲለብሱ፤ሴቶች “መሸኮ” ከወገብ በታችና ከጉልበት በላይ ያለውን የፊት ለፈት ሰውነቷን የሚሽፍን ቆዳ፣ ከጥምራ ዛፍ ቅርፊት ልጣጭ የውስጠኛውን ያቀልሙና ያገለድማሉ። ከቆዳ ሌላ እናቶች እጅ ጉርድ ጥብቆ ቀሚስ ይለብሳሉ፡፡
                                                            የአባቶች አለባበስ
                                                      ባህላዊ የለቅሶ ሥርዓት
ማቹ በሀገሩ ታዋቂና ጀብዱ የሠራ ከሆነ ዕድሩ ከላካቸው መልዕክተኞች ሌላ የሟች ወገኖች ለነሱ የለቅሶ አዋጅ ነጋሪዎች/ በየሀገሩና በየአካባቢው በየገበያ ቦታ እንዲዞሩ ይደረጋራል፡፡ በሽለላና ፉከራ ታዋቂ የሆኑትን ግለሰቦች በመመልመል የሟችን የዘርሀረግ እና ሀብቱን ብዛት፤ የነበረውን ሹመት፣ ጉብዝናውንና ጀብዱን እየዘረዘረ የነብርቆዳ ለብሰው የአንበሳ ሥዕል ጦርና ጋሻ ይዘውና የንስር ላባ በፀጉራቸው በመሰካት ገበያ ወደ ሚቆምበትና መንገዶችና አካባቢዎች የሰማሉ፡፡ በሟች ቤት ከፍተኛ ድግስ ተደግሶ ለቅሶ ጠሪዎችና መልዕክተኞች ተጋብዘው ድግሱን እንዲበሉ ይደረጋል፡፡ ለቅሶ ሲጀምር ነጋሪት ይጐሰማል፡፡
ነጋሪት ለሚጐስመው ገንዘብ ይከፈለዋል፡፡ ምግብና መጠጥ ይሰጠዋል፡፡ ነጋሪት የሚመታው የባህላዊ ለቅሶን ዜማ በሚያጅብ ሁኔታ ሲሆን ነጋሪቱ ያለበት ቦታ ለመድረስ ሴቶች ከፍተኛ ውድድር ያደርጋሉ፡፡ ትርዒትም ያሣያሉ፡፡ እንደኛዋ ከቀደመች ሌላው እሷን ገፍትራ ጥላ ለማለፍ ትፎክራለች፡፡ ጉልበት የሚጠይቅ በመሆኑ ፈታኝ ነው፡፡ የቀብር ጉድጓድ የሚቆፈረው ለአባት የሚች ታላቅ ልጅ ለሚስት ደግሞ ባል ቀድሞ ከወጋ በኋላ ነው። የሚቆፈርበትን ቦታ በግራ እጅ ሶስት ጊዜ ይወጋል፡፡ በወጋበት ቁጥር የአባቱን ንብረት በስም እየጠራ በዚህ ውጋው በማለት በዙሪያ ለተሰበሰቡ ሰዎች ያሰማል። በብሔረሰቡ በህግ መሠረት እነዚህ የተጠሩ ንብረቶች በንብረት ክፍፍል ጊዜ ክቁጥር ሣይገቡ ለዚህ ታላቅ ልጅ የሚሰጡ ናቸው፡፡
በሟች ቀብር ዙሪያ የቅርብ ዘመዶች የተለያዩ የዛፍ ዝሪያዎች በመትከል ይንከባከባሉ፡፡ ከሟች ወንድ ልጆች አንዱ የሟችን ስም እየጠራ ይህ የኔ ስጦታዬ ነው እያለ በመመረቅ በዙሪያው ወተት ያፈሳል፡፡ አብሮት ያሉ ሌሎች ሰዎች አፈሩ ይቅለልህ፣ ከግራ ከሆንክ ወደቀኝ ይመልስ በማለት ይመርቃሉ፡፡ ወተቱን የሚያፈስው ከግራና ከቀኝ ፣ ከራስጌና ከግርጌ እያሣለፈ ምርቃቱ ያጅባል፡፡ ይህ ሥርዓት የትኩስ ወተትና ማር የማፍሰስ ሥርዓት “ጨዲሻ' ተብሎ ይታወቃል፡፡
በሴቶች ሞት ለቅሶ ሥርዓት ላይ አዋጅ ነጋሪና መልዕክት አስተላላፊ አይኖርም፡፡ ለወንዶች የሚገጠም የለቅሶ /ሙሾ/ ግጥም በሴቶች አይገጠምም፡፡ ለሴቶች ነጋሪትም ሆነ ከበሮ አይመታም፡፡ ብዙ ትኩረት ተሰጥቶ የሚለቀሰው የሟቿን የዘር ሐረግ ጥረት፣ ሙያዋ እንግዳ ተቀባይነቷ የሰውነት አቋሟና እየተዘረዘረና እየተገጠመላት ይለቀሳል፡፡ በከምባታ ብሔረሰብ ሕፃን ሲሞት እንደ አዋቂ መሪር ሃዘን አይኖርም፡፡ ሞተ ተብሎ አይነገረም ሕፃኑ ጠፋ ይባላል፡፡ ለብዙ ዘመድ አይላክም ቀብሩ በዕለቱ ይፈፀማል።