ማረቆ
የማረቆ ብሔረሰብ
የማረቆ ብሔረሰብ በዋነኛነት ስፍሮ የሚገኘው ማረቆ ልዩ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ የብሔረሰቡ አባላት በዋናነት በ1 የከተማ አስተዳደር፣ በ24 የገጠር ቀበሌያትና በ2 የከተማ ቀበሌያት የሚኖሩ ሲሆን የልዩ ወረዳዋ ዋና ከተማ ቆሼ በመባል ትታወቃለች፡፡የልዩ ወረዳዉ አጠቃላይ ህዝብ ብዛትም ወንድ 48,735 ሴት 45,953 በድምሩ 94,688 እንደሆነ ይገመታል፡፡
የልዩ ወረዳው መልክአምድራዊ አቀማመጥ በአብዛኛው ሜዳማ ሲሆን የአየር ንብረቱ ደግሞ ቆላማ ነው። የብሔረሰቡ ዋነኛ መተዳደሪያ ጥምር ግብርና ሲሆን በዋናነት በርበሬ፣ በቆሎና ጤፍ ለፍጆታና ለሽያጭ ሲያመርት የማረቆ አርሶ አደር በበርበሬ ምርቱ በብሔራዊ ደረጃ ይታወቃል። ክእርሻ ሥራው ጐን ለጐን የቀንድ እና የጋማ ከብቶችን ፍየሎችና በጐችን ያረባል፡፡ እንዲሁም ከእንጨት፣ ከብረት እና ከቆዳ የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን በማምረት ለተለያዩ አገልግሎቶች ይጠቀማል።
ቋንቋ
የብሔረሰቡ ቋንቋ ሊቢድኛ/ማረቆኛ/ ከምስራቅ ኩሺቲክ የቋንቋ ቤተሰብ የሚመደብ ሲሆን ከሀድይኛ፣ ከምባትኛ፣ሲዳምኛ፣ ጌድኦኛ፣ ቀቤንኛ፤ቡርጂኛ እና ጠምባሮኛ ቋንቋዎች ጋር ይቀራረባል፡፡ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የብሔረሰቡ አባላት ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ ኦሮምኛ፣ ሀድይኛ፣ ጉራግኛ እና ስልጢኛ ቋንቋዎችን ለመግባቢያነት ይጠቀማሉ፡፡ ቋንቋውን ለማሳደግና የጽሁፍ ቋንቋ ለማድረግ ቀላል ሊብድኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት" በአቶ ወንድሙ ኤርገዶ (2006 ዓ.ም)፣ “የማረቆ ብሔረሰብ ባህላዊ ታሪክ" በብሔረሰቦች ምክር ቤት (2003 ዓ.ም)፣ የማረቆ ባህላዊ እሴቶች በተመለከተ (2007 ዓ.ም) ተሰርተው ስነድ ለብሔረሰቡና ለሚመለከታቸው ተቋማት ተሰራጭቷል፡፡
ታሪካዊ አመጣጥና አሰፋፈር
ከተለያዩ ታሪካዊ ፅሁፎችና ከአንጋፋ የብሔረሰቡ ተወላጆች የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የብሔረሰቡ ታሪካዊ አመጣጥና አስፋፈር በእጅጉ ከሀድያ ብሔረሰብ አመጣጥና አሰፋፈር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የብሔረሰቦች ም/ቤት ያስጠናው የማረቆ ብሔረሰብ ባህላዊ-ታሪክ ጥናት ጽሑፍ (2005 ዓ ም) ይህንን ሀቅ ያጠናክራል፡፡ ከኩሽ ጠዘቦች ታላላቅ እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ የብሄረሰቡ አባላት በምስራቁ የሀገሪቱ በሀረር በድሬዳዋ ገደብሰሬ እና አርሲ አሰላ አካባቢ በተለያዩ ጊዜያት ከሰፈረ 124 ብሔረሰቡ በባህሪዉ አርብቶ አደር በመሆኑ ግጦሽና ዉሃ ፍለጋ በተለያዩ አካባቢዎች ሲዘዋወር ቆይቶ በመጨረሻም አሁን ባለበት አካባቢ እንደሰፈረ ይነገራል፡፡ ማረቆ ብሔረሰብ የተገኘባቸው ሁለቱ የሀድያ ልጆች /የዘር ሃረጎች ቡቼና ጉፍታሞ የሚባሉት አባቶች ሲሆኑ፤ በውስጣቸው 64 ጎሣዎች / ማህበራዊ ቡድኖች/አሏቸው፡፡ የእነዚህ 64 ጎሣዎች ዋና ዋና መሠረቶች /ግንዶች ማዩ፤መንሱሮ፣ኡዳሞ እና አገቤሎ ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ከአራቱ ግንዶች በመቀጠል ለ64ቱ ጎሣዎች መገኘት በቅድሚያ የሚጠሩት አሌ፤ አጃኔ፣ ገሾ፣ ዌረራ፣ ሀሌቦ፣ ማዬ፣ ኦዶሮ፣ ኮንታማ እና ኬቶ ናቸው፡፡
ባህላዊ አስተዳደር
ብሔረሰቡ የራሱ የሆነ ነባር ባህላዊ አስተዳደር ያለው ሲሆን የተለያዩ የስልጣን እርከኖችና የስራ ሐላፊነቶች ያሉበት ነው፡፡ወለብገራድ /ንጉስ/ የባህላዊ አስተዳደሩ ቁንጮና የበላይ ሲሆን ሥልጣኑም በዘር ሃረግ ከአባት ወደ ልጅ የሚተላለፍ ነው፡፡ ዋና ተግባሩም ሕዝቡንና የበታች የስልጣን አካላትን በበላይነት መምራት ሲሆን የአስታራቂነት ሚናውም የጎላ ነው፡፡ ከንጉሱ በታች ድልገራድ እና ሃድገራድ የሚባሉ ሣዎችን የሚመሩ መሪዎች አሉ፡፡ ተግባራቸውም የየራሳቸውን ጎሣ መምራትና የወለብ ገራዱን /የንጉሡን/ ዉሳኔ ማስፈፀም ነው፡፡ ጂምአዲላ በተወሰነ አካባቢ (መንደር/ የተወሰነ ሥልጣን ያላቸው የሕዝብ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ገፅጥአና የሚባሉ አካላት ደግሞ በጎሣው አባላት የሚመረጡ የጦር አበጋዞች /መሪዎች/ ሊሆኑ ለብገራድ /ንጉስ/ትዕዛዝ በመቀበል ሕዝቡን ለጦርነት ያዘጋጃሉ፡፡
በብሔረሰቡ የእርቅና የዳኝነት ስራዎችን ለማከናወን ከእያንዳንዱ ጎሣ ታዋቂ የሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች ይመረጣሉ፡፡ የሽማግሌዎች ሽንጐ "ዱሚቾ" በመባል ይታወቃል፡፡ ባህላዊ አስተዳደሩ የነፍጠኛው የአገዛዛ ስርዓት በተንሰራፋበትም ወቅት በመንግስት ስር ሆኖ በጎሣ መሪዎች ሲመራ እንደነበር ይነገራል፡፡ ብሔረሰቡ በመካከሉም ሆነ ከሌሎች አጐራባች ብሔረሰቦች ጋር ለሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶች በባህላዊ መንገድ ዳኝነት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ብሔረሰቡ ከአጐራባቹ ጋር አለመግባባትና ግጭት ውስጥ ሲገባ ሀፉ/ጥላ/ በተባለ ባህላዊ የዳኝነት መስጫ ስፍራ መሪዎችና የሀገርሽማግሌዎች ዱሚቾ/ሸንጎ/ በመስባስብ ችግሩን በመፍታት ግጭቱ እንዳይባባስ በእርቅ ይቋጩታል፡፡ በዳዩ ክፍል ለተበዳዩ ካሣ ይከፍላል፡፡ ግጭቱ በብሔረሰቡ አባላት መካከል ከሆነ ግን ካሣ መብላት እንደ ነውር ይቆጠራል። የብሔረሰቡ አባላት ከአጎራባች ብሔረሰቦች ጋር ክተገዳደሉ ደግሞ ክሁለቱም ወገኖች ዝምድና የሌላቸው አገናኝ ሽማግሌዎች ይላኩና መማማያ/ጉዳ/ ጥቁር ፍየል ቀርቦ የአንደኛው ብሔረስብ በጉን ሲያርደው የሌላኛው ብሔረሰብ ደግሞ ሆድ እቃውን ይሰነጥቅና አንጀቱን ያወጣዋል፡፡ ከዚያም የሁለቱም ወገኖች የእግር አውራ ጣት በፍየሉ አንጀት ይታሰርና ለወደፊቱ ላለመበቃቀልና በቤተሰብነት ለመተያየት የጉዳ ቃለ መሐላ ፈጽመው እርቀ ስለም ይወርዳል፡፡
የማረቆ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት
ብሔረሰቡ ከአጎራባች ብሔረሰቦች ጋር አለመግባባትና ግጭት ውስጥ ሲገባ የጋራ የእርቅ ኮሚቴ በማቋቋም ችግሮችን ይፈታል፡፡ ይሁን እንጂ ከአጎራባች ብሔረሰቦች ጋር የሚጋራቸው የተለያዩ ባህላዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ስላሉት በመቻቻልና በመረዳዳት አብሮ ከመኖር ባሻገር የከረረ ግጭት ውስጥ አይገባም። ጊዜያዊ ግጭቶ ቢኖሩም ችግሮች ስር ሳይሰዱ ወዲያዉኑ በባህላዊ ስርዓት እርቅ ይፈጠራል።የማረቆ ብሔረስብ ብሔራዊ ህልዉናዉን የሚጋፉትን ኃይሎች ባጋጠሙት ጊዜ ለማንነቱና ለነፃነቱ ተጋድሎ ሲያደርግ ቆይቷል። ባለፉት አስከፊ ስርዓቶች ሀገሩን ከዉጭወራሪዎች ለመከላከል በማይጨው ጦርነት መሳተፉን ከጽሁፍና ከትውፊት የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። በባህላዊ አስተዳደሩ ምንም አንኳን የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ የነበረ ቢሆንም በጦርነት ጊዜ ከወንዶች ጋር አብረው ከመሰለፋቸውም ባሻገርጦሩ በድል እንዲመለስ ግቻ እየቋጠሩ ፈጣሪቸዉን በፀሎት ይለምኑ እንደነበርከታሪክ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ባህላዊ ዕሴቶች
የጋብቻ ሥርዓት
ማረቆ ብሔረሰብ የራሱ የሆኑ የተለያዩ ባህላዊ መገለጫዎች አሉት፤ ከመገለጫዎቹ ካስል እንዱ ጋብቻ ነው። በብሔረሰቡ ነባር የጋብቻ አፈፃፀም ሴቶች ከ15-17 ወንዶች ደግሞ ከ16-20 ዓመት ሲደርሱ ጋብቻን የሚፈጽሙ ሲሆን በርካታ የተለመዱ የጋብቻ አፈፃፀም አይነቶችም ይተገበራሉ፡፡ ጠዋጂ /በቤተሰብ ስምምነት መተጫጨት የሚፈፀም ጋብቻ/ ወንዱ ወጣት ለጋብቻ የፈለጋትን ልጅ ለቤተሰቦቹ ሰውቆና አሳጭቶ የሚፈፀም ጋብቻ ነው፡፡ ኡሉሊማ" /ደንገተኛ/ ድንገት ኮሳንቾ ገባ የሚባለውና አግቢዉ ጓደኞቹን በመሰባሰብ ልጅቷ መኖሪያ ቤት ገብቶ በመቀመጥ እና በማስገደድ የሚፈፀም ነው፣ 'ጉስኖ ጠለፋ/ ወጣቱ ለሚስትነት ያሰባት እና የምትመጥነው ልጃገረድ አለመታጨቷን ካረጋገጠ በኋላ ልጅቷን በሃይል በመጥለፍ የሚፈፀም ጋብቻ ነው፡፡ "ሔሪማ" /ማባበል/ ተጋቢዎች ሳይገናኙ እና ሣይተዋወቁ የልጁ ወገኖች ወይም ሌሎች ሦስተኛ ወገኖች ለሙሽራዋ ስለአግቢዉ ጥሩ ጥሩውን እየተናገሩ ካሳመት በኋላ የሚፈፀም ጋብቻ ነው፡፡
'አጋባዲማ" /ወደገባ/ ሙሽራዋ በራሷ ተነሳሽነት ለባልነት ወደ መረጠችው ልጅ ቤት በመሄድ “ልጃችሁን ወድጄዋለሁ" ብላ በቤቱ ምስሶ ላይ ትጠመጠማለች፡፡ የልጁ ወላጆችም የማንፃ "ጭዳ አርደው እርሷንም በክብር ተቀብለው ጋብቻው ይፈፀማል፡፡ 'ሚዕንበቶማ" /የምትክ ጋብቻ/ በትዳር ሕይወቱ ጥሩ የነበረ ባል የትዳር አጋሩ ከሞተችበት የሟች እህት “እንባውን ትጥረግለት ልጆቹንም ታሳድግለት” ተብሎ በምትክ ትሰጠውና ጋብቻቸውን ይፈጽማሉ፡፡ "ለጎቴ˚ /የውርስ ጋብቻ/ ባል ሲሞት ሚስቱ የሃዘን ግዜዋን ስትጨርስ የመጨረሻው ታናሽ ወንድሙ ልጆቹን ያሳድግለት ተብሎ የወንድሙን ሚስት እንዲወርስ ተደርጎ የሚፈፀም ጋብቻ ነው፡፡
ከላይ ከተቀመጡት የጋብቻ አይነቶች "ጠዋጅ ወይም በቤተሰብ ስምምነት የሚፈፀመው የጋብቻ አይነት አፈፃፀሙ ከባህላዊ እምነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በመጀመሪያ ሙሽራው ትመጥነኛለች ብሎ ያሰባትን ልጃገረድ ሊያጫት መፈለጉን በጓደኞቹ አማካኝነት ለቤተሰቦቹ ይገልፃል፡፡ ከቤተሰቦቹ አዎንታዊ ምላሽን ካገኘ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን የማጨቱን ስራ ይጀምራል፡፡ ጓደኞቹም ጦራቸውን ይዘው በማለዳ ወደ ልጅቷ ቤተሰብ ቤት በመሄድ ጦራቸውን በራፍ ላይ አቁመው ወደ ቤት ይገቡና ሰላምታ ሳይሰጡ ለተወሰነ ደቂቃ ከተቀመጡ በኋላ ወጥተው ይሄዳሉ፡፡ ይህ ድርጊት ለሦስት ተከታታይ ቀናት ይቀጥላል፡፡ ነገር ግን እርብ እና ረቡዕ በብሔረሰቡ ደረቅ ቀናት ናቸው ተብሎ ስለሚታሰብ በእነዚህ ቀናት ወደ ልጅቷ ቤተሰቦች አይኬድም።ለማጨት በሚሄዱበት የመጀመሪያው ዕለት የሚያጋጥሟቸዉን ገዶችም በአትኩሮት ያስተውላሉ፡፡
"ጣራዕሌ” የተባለች ወፍ ከአጭዎች በስተግራ እየጮኸች ከሄደች፣ እንስራ ሙሉ ውሃ የተሸከመች ሴት ካጋጠመቻቸው፣ አቦል ቡና ሲጠጣ፣ ወተት ሲታለብ ወይም ሲናጥ እና የጋጣ አዛባ ሲወጣ አጭዎች ወደ ልጅቷ ቤት ከደረሱ ሙሽሮቹ ገዳቸው ገጥሟል መልካም ትዳርም ያጋጥማቸዋል ተብሎ ይታመናል ነገር ግን ይቺው ገድ አመላካች ወፍ/ጣራዕሌ/ ካጭዎቹ በስተቀኝ ከጮኸች፤የአጭዎችን የቀኝ እግርእንቅፋት ከመታቸው፣ አጭዎች በጉዟቸው ባዶ እንስራ የያዘች ሴት እና በመጥፎ ስም የሚጠሩ ስዎች ካጋጠሟቸው እና ለመታጨት የተመረጠችው ልጃገረድ ቤት ስትጠርግ እና አመድ ስታወጣ አጭዎቹ ከደረሱ “ወፍ ሰላልስጠን ገዳቸው ጥሩ አይሆንም ተብሎ ስለሚታመን የማጨቱ ሂደት ይቋረጣል፡፡
አጭዎቹ በማጨቱ ሂደት ከተሳካላቸው /ወፍ ከቀናቸው/ "ልጃችሁ ልንሆን ወላጆቻችን ልትሆኑን መጥተናልና እኛ ባስተዋልነው እናንተም ባረጋገጣችሁት መሠረት ወፍ ሰጥቶናልና ልጃችሁን ስጡን" በማለት የልጁ አባት ወይም ተወካይሆኖ ልጅቷን የሚያጭ ሰው የልጅቷን እናት ይጠይቃል፡፡ የልጅቷ እናትም ለተወሰኑ ቀናት ጥናት አድርጋ ወፍ ከሰጠቻት/ገዱ ከቀናት/ ከልጅቷ አባት ጋር ተመካክራ አዎንታዊ ምላሽ ከሰጠች ለማጨት የመጣው ሰው ከተቀመጠበት ተነስቶ ትከሻዋን ይስማታል፡፡ቀጥሎ የሚጠበቀው የልጅቷ አባት ፈቃድ ስለሆነ ሌሎች ቤተዘመዶችንና ጎረቤቶችን ጨምሮ ከደጃቸው ባለው ዛፍ ጥላ ስር ተቀምጠው ቀደም ሲል ከታዩት ገዶች መካከል በጥቂቶቹ ክትትል ተደርጐ ከተሳካ የእናት መልካም ፍቃድ ላረፈበት ጋብቻ አባት አሉታዊ ምላሽ ስለማይሰጥ የጋራ ስምምነቱ ይፀድቃል፡፡ የአባት አዎንታዊ ምላሽ ከተሰማ በኋላ አጭዎች የአባትን ትከሻ ይስሙና ቀጣዩን የጋብቻ ጥያቄያቸውን ደግሞ ለልጅቷ አጎት ያቀርባሉ፡፡ አጉትዬውም የጋብቻ ጥያቄው ለክብሩ ሲባል ወደሱ መላኩን ስለሚረዳ ‹‹ እናት አባቷና ወፍ ከሰጠቻችሁ እኔም በጋብቻው ተስማምቻለሁ› በማለት ይስማማል። በመጨረሻም የአጎትዬውን በጋብቻው የመስማማቱ ምላሽ ለልጂቷ ቤተሰቦች ይነገርና የፍጥምጥም /ጎሜኦ/ ለማድረግ ቀነ ቀጠሮ ይያዛል። ድግስ ይደገስና ጥሎሽ ወይፈንና ጊደር ለአባት ይሠጣል፡፡ ለአጐት ለእናት ተብሎ እንደየድርሻቸው ይሰጣቸዋል፡፡ "ጊጊዮ™ መሸኛ ተብሎ ከብት፣ ትራስ፣ቅቤ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ለሙሽሪት ይሠጣሉ፡፡
ባህላዊ በዓል አከባበር
ብሔረሰቡ የተለመዱ ባህላዊና መንፈሳዊ በዓላት አሉ፡፡ ከፈጣሪው ለተደረገለት መልካም ነገር ምስጋና የሚያቀርበውና በልጁም ሆነ በሀብቱ ችግር ሲያጋጥመው ለአምላኩ የሚሳለው ጠጅ/ዲቃሳ/ እየጠጣ ነው። የቀደምት አባቶቹን የሙት መንፈስ እና የፈጣሪውን ስም እየጠራ ስኬቱን በማውሳትና በማወደስ ለቀጣዩ በጎ ነገርእንዲገጥመው እየተመኘ ሌሊት ሲሆን ገንፎ ተዘጋጅቶለት ጠጅ እየጠጣና እየሸለለ አምልኮታዊ ስነስርዓቱን ይፈፅማል፡፡ የዚህ ባህላዊ የበዓል አከባበርም “ኢዶት አልዋት" ሉባ ይባላል፡፡በብሔረሰቡ በእስልምና ተከታዮች ዘንድ የኢድ አልፈጥርEዕሙሳ/ የመውሊድና የአረፋ በዓላት የሚከበሩ ሲሆን ክርስቲያኖች ደግሞ ዘመን መለጠጫ፣ መስቀልና ገናን ያከብራሉ። ዋሬ የሚባል በየ15 ቀነ- ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ የሚከበር የእስልምና ተከታዮች በዓልም ተጠቃሽ ነው፡፡
ብሔረሰቡ ጀግኖችን ለማወደስ፣ለሠርግ፣ለጦርነት፤ለስራ ወዘተ... የተለያየ ይዘት ያላቸው ዘፈኖችና ጭፈራዎች አሉት፡፡ የብሔረሰቡ አባላት በዕድሜ ደረጃና በጾታ ተከፋፍለው ለተለያዩ ማህበራዊ አውዶች የሚውሉ ዘፈኖችን እየዘፈነ ይጨፍራሉ፡፡ ጭፈራዎቹንም ከበሮ በመምታት በእጃቸው በማጨብጨብ እና እግራቸውን ተራ በተራ አንስተው መሬቱን በመምታት ያደምቋቸዋል፡፡ ቀደም ባሉት አባቶቻቸው ጊዜ ዝላይ፣ የገበጣ ጨዋታ፣የፈረስ ጉግስ፣ ጉምብቻ/ትግል/ ለእረፍት ጊዜ ማሳለፊያነት ይጠቀሙባቸው ነበር፡፡
ባህላዊ የቤት አሰራር
ብሔረሰቡ ቀደም ባሉት ዓመታት ከከብት አርቢነቱ ጋር በተያያዘ ለከብቶች ምቹ የግጦሽ ሳርና ውሃ ለመፈለግ ከቦታ ወደ ቦታ ይንቀሳቀስ ስለነበር ክዝናብና ከፀሀይመከላከያነት ያለፈ ውበት ያለውንና ጠንካራ ቤት አይሰራም ነበር። ከቅርብ ዓመታት. ወዲህ ግን ከእንጨት የተዋቀረና ማገር በልጥ የተሰራ ግድግዳ እና "ባንቾ በሚባል ቀጫጭን ማገር ተጠላልፎ ጣራ ተሰርቶለት በሣር በመክደን መኖሪያቸውን ይሠራሉ። እንዲሁም ደግሞ መካከሉ ላይ ምስሶ ይቆም እና ጣራው ተገድግዶ የአካባቢውን እንቅስቃሴ በሚያሣይ መልኩ ሳር በማልበስ የሚሰራ የቤት አሰራርም በብሔረሰቡ ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ የዚህ አይነት የቤት አሰራር አባወራው ሙቀትና ምቾት አግኝቶ ከበረት ያሉ ከብቶች በሌባ እንዳይሰረቁ በንቃት ለመከታተል እንዲያስችለው ታስቦ የሚሠራ ነው፡፡ ከእጎራባች ብሔረሰቦች የቤት አስራር ተሞክሮ በመከፋፈል መሥራት በመለማመድ ላይ ናቸው፡፡
ባህላዊ ምግብ
ብሔረሰቡ ዘንድ ጠዋትና ማታ በቤት ደጃፍ ላይ በጋራ በመቀመጥ የመመገብ ልማድ አለ። አበቶሎ የሚዘጋጅ ቀጣ፣ ወተትና ዐይብ፣የገብስ ገንፎ በቅቤና ቡላ በቅቤ የብሔረሰቡ ባህላዊ ምግቦች ናቸው፡፡ ባህላዊ መጠጣቸው ደግሞ የማር ውጤት ነው: የማር ውጤት በቀንድ ዋንጫ ሲጠጣ ወተት ለውሃ ጥም እና ለምግብነት ዘወትር ይጠጣሉ፡፡
ባህላዊ አለባበስ
የሊቢዶ ማረቆ ብሔረሰብ የራሱ ነባር የአለባበስ ሥርዓት የነበረው ሲሆን ለሌሊት ልብስነት ቡሉኮ /መዝ/ እና ከስንጋ ቆዳ የተሰራ "ገባልኦ" ይጠቀም ነበር። የቀን ልብሳቸው ደግሞ ሴቶች ከለፋ የከብት ቆዳ የተዘጋጀ “ቂጣ" የሚባል ቆዳን ዋልጢሻ የተባለ መታጠቂያ ይጠቀሙ የነበረ ሲሆን አሁን አሁን ግን ወጣቱ ትውልድ በፋብሪካ የተመረቱ አልባሣት ይጠቀማል፡፡ ወንዶች የቆዳ ግልድማቸውን ትተው ከአቡጀዲና ከመርዱፋ በእጃቸው የተሰፉ ተነፋነፍ ሱሪዎችን ሲለብሱ ለአላባሽነት ደግሞ ቡልኮ ወይም ጋቢ ይጠቀማሉ፡፡ ህፃናት ግን ከፍየል ቆዳ ወይም ከአቡጀዲ የተሰራ ቅድ ሽሚዝ ይለብሳሉ፡፡
የለቅሶና የሃዘን ሥርዓት
የማረቆ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ የለቅሶ ስርዓት አለው፡፡ ታዋቂ እና ወንዶች የብሔረሰቡ አባላት ሲሞቱ " አረጂ ወይም መርዶ የሚያረዳ ሰው በየአቅጣጫ በፈረስ ይላካል። ሰውየው መሞቱን የሰሙ ቤተመዶችም "ሆሌ መንቾ ሆሌሞራ" እያሉ ወንዶች በፈረስ ሴቶች ደግሞ በእግር ሆነው ባራሞ፣ኪላሞ፣ ኢጃራሞ፤ወዘተ እያሉ የአባቱ ስም እየተጠራ ይለቀስለታል። በብሔረሰቡ ታዋቂ የቤት እመቤት ስትሞት ደግሞ 'ባሮባንደሬ፣ድልቤ ባንደፊ” እየተባለ ይለቀስላታል። የአባቷ ስም ግን እንደ ወንዶች ለማስለቀሻ አይጠራም ያገባች ሙሽራ ስትሞት "ባሮ ኢዳቼ" ለማግባት የታጨች ልጃገረድ ስትሞት ባሮ ቃጠሜ" እመጫት ስትሞት ደግሞ 'ባሮ ስቻሜ" እየተባለ ይለቀስላታል።
በለቅሶው ስነስርዓት አስለቃሾች ሴቶች የጎንዮሽ ረድፍ ይስለፉና ፊት ለፊት እግሮቻቸውን ተራ በተራ እያነሱና ጆሮ ግንዳቸዉን በእርምጃቸው መጠን በሁለቱም እጆቻቸው እያስነኩ ወደ ለቀስተኛዉ ይገባሉ፡፡ ለቀስተኛ ሴቶችም እንደ አስለቃሾች ጎንዮሽ ተሰልፈው "ሃይ ሃይ" እያሉ ይቀበሏቸዋል። አስለቃሾች ከለቀስተኞች መካክል ገብተዉ ስለሟቿ ውሎ፣ ሙያ እና ዝና በጠቅላላው ስለማንነታ በመግለጽ ሙሸ እያወረዱ ለቀስተኛውን ያስለቅሳሉ፡፡ ልጆችሲሞቱ ምንም አይነት የለቅሶ ስርዓት ላይደረግ ዘመድ አዝማድ ከያለበት ተሰብሰቦ የቀብራቸው ስርዓት ይፈፀማል። ሰው በሞተ በ12ኛው እና በ40ኛው ቀን ለህዘን ማብረጃ ቆጮና በቶሎ የተቀየጠበት ገንፎ ተዘጋጅቶ ይቀርብና "ማያስኮአ" እየተባለ ዘመድ አዝማድ ከተዘጋጀው ምግብ በጋርአብሮ ይበላል፡፡ ከሟች ቤተሰብ ሴት ልጅ ተመርጣ በግራና በቀኝ ውኃ እየረጨች 'ለቅሶ ይብረድ፣ሀዘንተኛው የተቀመጠበት ዳስ የሀዘን ዳርቻ ይሁን ካለች በኋላ ሽማግሌዎች መርቀው ዳሱ ይፈርስና የሃዘኑ ማሣረጊያ ይሆናል፡፡