ጉራጌ
የጉራጌ አጠቃላይ ገጽታ
የጉራጌ ዞን በክልሉ ውስጥ ከሚገኙት 7 መካከል ሲሆን በክልሉ ጉራጌ ዞንና ምስራቅ ጉራጌ ዞን ሆኖ በሁለት መዋቅር ተረዳጅቷል፡፡ ብሔረሰቡ ተወላጆች የሚኖሩበት ዞን በአብዛኛው ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚዋሰን ሲሆን በክልሉ ከሚገኙት ዞኖችና ልዩ ወረዳዎችም ከሀዲያና ከስልጤ ዞኖችና እንዲሁም ማረቆ ልዩ ወረዳ፣ከቀቤና ልዩ ወረዳና ከየም ዞን ጋር ይዋሰናል፡፡ የዞኑ የመሬት አቀማመጥ ሜዳማ፣ ተራራማ እና ሸለቋማ ሲሆን የአየር ንብረቱም ደጋ፣ ወይና ደጋና ቆላማ ነው፡፡ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ብሔረሰቦች ኢኮኖሚ የተመሠረተው በእርሻና በከብት እርባታ ላይ ነው፡፡ በ2016 ዓ.ም በክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ በተደረገዉ ፕሮጄክሽን የህዝብ ብዛት ትንበያ መሠረት ወንድ 884,787 ሴት 953,409 በድምሩ 1,838,196 እንደሚሆን ይገመታል፡፡
በጉራጌ ዞን ውስጥ በርካታ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶችና የቱሪስት መስህቦች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ፣የጥያ ትክል ድንጋይ አረቅጥ ሀይቅ፣መስቀል፣አንትሮሽት የእናቶች ቀን፣ዋልጋ ፏፏቴ፣ዳርጌ ፏፏቴ፣አርባን ዋሻ፣ሉቄ ፍል ላሃ፣ዛራ የተፈጥሮ ደንና ሌሎችም ተጠቃሾች ናቸዉ፡፡
የጉራጌ ብሔረሰብ
የጉራጌ ብሔረሰብ በዋናነት በጉራጌ ዞን በምስራቅ ጉራጌ ዞን ውስጥ ይገኛል። የብሔረሰቡ አባላት ካላቸው ተንቀሳቅሶ የመስራት ባህሪ አኳያ በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በአዲስ አበባ፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ ፣በአዋሳ ፣በዲላ፣ በናዝሬት፣ በጅማ እና በሌሎችም ከተሞች በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው ይኖራሉ፡፡ “ጉራጌ" የሚለው ቃል ለብሔረሰቡም ሆነ ብሔረሰቡ በዋናነት ለሰፈረበት አካባቢ መጠሪያ ሲሆን የቃሉ ስያሜ የብሔረሰቡ ቀደምት መነሻ ከሆነው በኤርትራ አካለ ጉዛይ አካባቢ ከሚገኘው “ጉርዓ" ከተባለው ቦታ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ብሔረሰቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ያረፈበት ቦታ "አይመለል" እንደነበረ የሚናገሩም አሉ፡፡ ብሔረሰቡ የሚኖርባቸው ወረዳዎች ሜዳማ፣ ተራራማና ሸለቋማ የመሬት አቀማመጥ ሲኖራቸው፤ የአየር ንብረታቸው ደግሞ ደጋ፣ ወይና ደጋና ቆላማነት ይንፀባረቅበታል።የብሔረሰቡ የኢኮኖሚ መሠረት ጥምር ግብርና ሲሆን በግብርናው መስክ ከተክሎች ጫት፣ እንሰት፣ ቡና፣ በርበሬ፤ ከብርዕ እህሎች በቆሎ፣ጤፍ፣ ስንዴና ገብስ፤ከጥራጥሬ አተር፣ባቄላ፣ ሽምብራ፣ ቦሎቄ፤ ከፍራፍሬ ብርቱካን፣ ፓፓያ፣ ማንጎ ፤አቡካዶ ከሥራ ሥር ድንች፣ ጐደሬ፣ ቦይና፣ ስኳርድንች ካሮት እና ቀይሥር የመሳሰሉት ይመረታሉ፡፡
ቋንቋ
የብሔረሰቡ ቋንቋ ከሴማዊ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ ሲመደብ ከትግርኛ፤ አማርኛ፣ ስልጢኛ፣ አደርኛ፣ ቋንቋዎች ጋር ይቀራረባል፡፡ ቋንቋው አስር ዘዬዎች (Dialects) አሉት፡፡ እዣ፣ ጌቶ፣ ሙህር፣ መስቃን፤ ዶቢ፤ ቸሃ፤ እንደጋኝ፤ ሶዶ ክስታኔ/፣ ወለኔ እና እነሞር በመባል ይታወቃሉ፡፡ ሌስላው የተባለ የቋንቋው ተመራማሪ የጉራጊኛን ቋንቋ ከቅርርብነታቸው አንፃር በሶስት ምድብ ከፋፍሎ፣ እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡፡ አንደኛ ምስራቅ ጉራጌ ወለኔ፣ሁለተኛ ምዕራብ ጉራጌ ቸሃ፣ እንደጋኝ፣ እነሞር፣ እዣ እና ጌቶ ሦስተኛ ሰሜን ጉራጌ ሶዶ ሲሆን ምሁር፣ መስቃን እና ዶቢ ከየትኛው የዘዬዎች ምድብ እንደሚካተቱ ለማወቅ ሰፊ የሆነ የቋንቋ ጥናት እንደሚጠይቅ አስምሮበታል፡፡ የእነዚህ ዘዬዎች መብዛትም ቋንቋውን ወጥ በሆነ መልኩ አደራጅቶ ለትምህርትና ለሥራ ቋንቋነት ለማብቃት አስቸጋሪ ሁኔታን እንደፈጠረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በቋንቋው ከተሰሩ የተለያዩ ስራዎች መካከል በዞኑ ባ/ቱ/መን/ኮሚንኬሽን የተዘጋጀ ወማካ (የቤተ ጉራጌ ምሣሌያዊ ንግግሮች)(2004 ዓ/ም)፣ በዞነ ባ/ቱ/መን/ኮም/ መምሪያ የተዘጋጀ እንቁዊት እንቆቅልሽ) ዊግና የቃል ዙምራ(ፉከራና ሽለላ) (2007 ዓ.ም) በዞነ ብ/ቱ/መን/ኮም/ መምሪያ የተዘጋጀ የጉራጊኛ ፊደል ገበታ ጥናት ሰነድ(2006 ዓ.ም) በዞኑ ባ/ቱ/መን/ኮም/ መምሪያ የተዘጋጀ አማርኛ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት(2008 ዓ.ም) በዞኑ ባ/ቱ/መን/ኮም/ወምሪያ የተዘጋጀ የጉራጊኛ ስርዓተ ነጥብ 2006 ዓ.ም) በዞነ ባ/ቱ/መን/ኮም/ መምሪያ የተዘጋጀ የጉራጊኛ ስርዓተ ጽህፈት(2006 ዓ.ም) ተጠቃሾች ናቸው። በአጐራባች አካባቢ የሚኖሩ የብሔረሰቡ አባላት ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ ቀቤንኛን፣ ኦሮምኛን፤ ማረቆኛን፣ ስልጢኛን፣የምሣን እና ሃድይኛን በተለያየ ደረጃ ለመግባቢያነት ይጠቀማሉ፡፡ በድንበር አካባቢ የሚገኙ የቀቤና፤ የኦሮሞ፤ የየም፤ የማረቆ፣ የሀዲያ እና የስልጤ ብሔረሰብ አባሎችም ጉራጊኛን በተለያየ ደረጃ ለተለያዩ ማህበራዊ ግንኙነቶች ይጠቀሙበታል፡፡
ታሪካዊ አመጣጥና አሰፋፈር
የጉራጌ ብሔረሰብ ከሦስት የተለያዩ ቦታዎች በተለያዩ ጊዜያት የመጣ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የመጀመሪያው ከኤርትራ አካለጉዛይ አካባቢ “ጉርዓ” ከተባለው ስፍራ አዝማች ስብሃት የተባሉትን መሪ ተከትለው እንደመጡና በአሁኑ ጊዜ ሰሜን ጉራጌ በተባለው አካባቢ እንደሰፈሩ የሚነገረው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከደቡብ አረቢያ ፈልሰው ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ በበርበራ በኩል አድርገው በመግባት ሐረርጌ ውስጥና ዝዋይ ሐይቅ አካባቢ የአረብ ዝርያ ያላቸው ጉራጌዎች እንደሰፈሩ የሚነገረው እና በሦስተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ደግሞ ከግራኝ አህመድ ወረራ ጋርተያይዞ ከሐረር አካባቢ የተነሳው የግራኝ ጦር አሁን ጉራጌ ዞን ከሚባለው አካባቢ ስፍሮ ቋሚ ኑሮውን እንደመሠረተና ጉራጌ የሚለውን ስምም እንደያዘ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ የተለያዩ የብሔረሰቡ ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና የጽሁፍ ሰነዶች የብሔረሰቡ መነሻ ከኤርትራ ወይም ደቡብ አረቢያ ነው በሚለው መሠረታዊ ሃሳብ ላይ ይስማማሉ፡፡
የጉራጌ ብሔረሰብ አሁን በዋናነት በሚኖርባቸው አካባቢዎች ቀደም ሲል "ያፈርስብ የሚባሉ ነባር ህዝቦች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ሕዝብ በኋላ የመጡት ሕዝቦች በሀብትም ሆነ በአስተዳዳር ብልጫ ስለነበራቸው በነባሩ ሕዝብ ላይ ተፅዕኖ በማሳደራቸው በነባሩ ሕዝብ የአኗኗር ስልት ላይ ለውጥ እንዳመጡ ሲነገር፣ የጉራጌ ሕዝብም የአዲሱና የነባሩ ሕዝብ መስተጋብር ውጤት ነው ተብሎ ይታመናል።
ባህላዊ አስተዳደር
የጉራጌ ብሔረሰብ የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችን የሚፈታበት አኵራ የሆኑ ባህላዊ እነዚህ ባህላዊ ደንቦች ወይም ሕጐች አሉት፡፡እነዚህም ባህላዊ ደንቦች ወይም ህጎች ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡና ዛሬም በስፋትና በጥልቀት የሚሰራባቸው ናቸው፡፡ ክዚህም የተነሳ የብሔረሰቡ አባላት ለባህላዊ አስተዳደሩ እራሳቸውን ስለሚያስገዙና በዋናነት ስለሚተዳደሩበት ብዙሀኑ አናሳውን አያጠቃም፤ አንዱ የሌላውን ሰላም አያደፈርስም!እንዱ የሌላውን ሀብትና ንብረት አይቀማም። በአጭሩ አንዱ የሌላውን መብት እንዲደፍርም ሆነ የሕግ ጥሰት እንዲፈጽም ባህላዊ መተዳደሪያ ደንቡ አይፈቅድለትም፡፡
የጉራጌ ብሔረሰብ የሚተዳደርባቸው ባህላዊ ደንቦች (ህጐች) በአደረጃጀታቸውና በአሠራራቸው ተመሳሳይ ቢሆኑም እንደየቤተ ጉራጌው የስም አጠራራቸው ይለያያል፡፡ከዚህ አንጻር በዋናነት የሚታወቁት አራት ሲሆኑ እነሱም :-
1. የሰባት ቤት ጉራጌ መተዳደሪያ ደንብ (የጉራጌ ቂጫ)
2. የሶዶና ወለኔ ቤተ ጉራጌዎች መተዳደሪያ ደንብ (የጐርደና ሴራ)
3. የመስቃን ቤተ ጉራጌ መተዳደሪያ ደንብ (የፈርአገዘኘ ሴራ)
4. የዶቢ ቤተ ጉራጌ መተዳደሪያ ደንብ (የዶቢ ጐጐት ስናኖ ሴራ)
ሲሆኑ እነዚህ ባህላዊ መተዳደሪያ ደንቦች(ሕጐች) በውስጣቸው የተለያዩ ጉዳዮችን የያዙ በርካታ ንዑሳን መተዳደሪያ ደንቦች እንዳሏቸው ይታወቃል፡፡ በጉራጌ ባህላዊ መተዳደሪያ ደንብ (ህግ) መሠረት በዳኝነቱ ሰርዓት የሚካተቱ ጉዳዮች በርካታ ሲሆኑ በዋናነት የነፍስ ግድያ፣የአካል ማጉደል፣የመግደል ሙከራ፣ የቤት ቃጠሎ፣ የሰብል ማቃጠል፣ መንቀልና መቁረጥ፣የስርቆትና የዘረፋ፣ የድንበር፤የወል የግጦሽ መሬትና የደን ክልሎች ለግል የማዋል፣ የጠለፋ ወንጀሎችና ሌሎችንም የመብት ጥሰቶችንና መተላለፍ ጭምር የሚዳኝበት ስርዓት ነው፡፡
በብሔረሰቡ የሚነሱ ግጭቶችና ወንጀሎች ደረጃና ባህሪ የተለያየ ከመሆኑ የተነሳ የሚዳኙትም በተለያዩ ባህላዊ አስተዳደር እርከኖች ወይም ሸንጐዎች ነው፡፡ አብዛኞቹ ግጭቶችና ማህበራዊ ችግሮች የሚዳኙትና መፍትሄ የሚያገኙት በዝቅተኞቹና በመለስተኞቹ የባህላዊ አስተዳደር እርከኖች ሲሆን በተለይ የነፍስ ማጥፋት፣ አካል ማጉደልና የግድያ ሙከራ ወንጀሎች የሚዳኙትም ሆነ አልባት የሚያገኙት በመሀክለኛው ወይም ቤተ ጉራጌ የሸንጐ አካል ሲሆን በዚህ ደረጃ ያልተፈቱና እልባት ያላገኙ ጉዳዮች የሚዳኙት በከፍተኛው የሸንጐ አካል ወይም ይግባኝ ሰሚ በሆነው የጉራጌ ባህላዊ ሽንጐ ነው፡፡ የብሔረሰቡ አባላት የደም ግጭትን ለመፍታት ኸተራት" ለተባለው ደንባቸው ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ ይህም በብሔረሰቡ አባላት መካከል በተከሰተ ግጭት ሰው ቢሞት የሟች ወገኖች በቁጭት ተነሳስተው በገዳይ ወገኖች ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝሩና ሌላም ጥፋት እንዳይከተል በማሰብ ከሟችና ከገዳይ ወገኖች ውጭየሆኑ ሽማግሌዎች እስከ አያት ድረስ ያሉት የገዳይ ወገኖች ቀያቸውን ለቀው እንዲወጡና ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ የእንባ መጥረጊያ ካሳ ይዘው እንዲመጠ የሚያደርጉበት የማጭት ማብረጃና የእርቅ መፈፀሚያ ስርዓት ነው፡፡
የጉራጌ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት
ከአጐራባች ብሔረሰቦች ጋር ግን ፤ በጋብቻ፣ በእቁብ፣ በእድርና በተለያዩ ማህበራዊና ባህላዊ ጉዳዮች የጠነከረ ግንኙነት ስላለው ተስማምቶ፣ ተፈቃቅዶና ተረዳድቶ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ሕልውናውን እና ማንነቱን ከሚፈታተኑት ኃይሎች አና የሀገሩን ዳር ድንበር ለመድፈር ከቃጡ ወራሪዎች ጋር ታሪካዊ ተጋድሎ አድርጓል። ለአብነትም ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመሆን ክጣሊያን ወራራ ኃይሎች ጋር፤ በፊውዳሉ ሥርዓት በተለይም በዘመነ መሳፍንት እና ከሚኒሊክ ተስፋፊ ጦር ጋር ያደረጋቸው ታላላቅ ተጋድሎዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ባህላዊ እሴቶች
የጋብቻ ሥርዓት
የጉራጌ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ የጋብቻ፣ የሃዘን እና የለቅሶ የበዓላት አከባበር! በብሔረሰቡ የተለመዱ የአመጋገብ፣ የአለባበስ እና የቤት አሠራር ስርዓቶች አሉት፡፡ መፈቃቀድ የሚፈፀም ጋብቻ የልጁና የልጅቷ ቤተስቦች ጋብቻውን ሲፈቅዱ የሚፈፀም ሲሆን የብሔረሰቡ ሕጋዊና ዋነኛው ጋብቻ ነው፡፡ ጠለፋ /ዝማጀ/ ጋብቻ የጠለፋ ጋብቻ በብሔረሰቡ የማይደገፍ በመሆኑ በጥሎሽ ወቅት ጠለፊው ከባድ ቅጣት ይጠብቀዋል። የድንገተኛ /መሪ/ጋብቻ በአንዳንድ አካባቢ ወጣቱ ጓደኞቹን ይዞ ወደ ልጅቷ ቤተሰብ ቤት እየተከለከለም ቢሆን ሰተት ብሎ ገብቶ አልወጣም ይላል። ሽማግሌዎቹም ከኋላ ተከትለውት ይገባሉ፡፡ በመጨረሻም አስፈላጊውን የጥሎሽና መሰል ሥርዓቶችን ክፈፀሙ በኋላ ኮረዳዋን ይዞ ይሄዳል እንጂ አይከለከልም፡፡ ምክንያቱም ዘራችንን ብሎ የመጣን ሰው መከልከሉ ጡር ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ የውርስ ጋብቻ በዚህ ዓይነት ጋብቻ የሚፈፀመው ባሏ የሞተባት ሴት ሀዘኗን ስትጨርስ /በተለይ የወለደች ከሆነች/ ቤተሰቦቿ ፈቅደውላት የባሏን ወገን የቅርብ ዘመድ ታገባለች፡፡
ከወንዱ ወገን የተመረጡ ሽማጌሌዎች ወደ ልጅቱ ቤተሰብ ይላካሉ፡፡ ሽማግሌዎቹም የናንተን ዝምድና ስለፈለግን ልጃችሁን ለልጃችን እንድትሰጡን በማለት በተለሳለሰ ሁኔታ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ የልጅቷ ወገኖችም አንዳንድ ነገሮችን ለማጣራት ያመቻቸው ዘንድ ከቤተዘመድ ጋር መክረን ምላሽ እንሰጣችኋለን በማለት ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ ይሰጣሉ፡፡ ከተደጋጋሚ ቀጠሮና ምልልስ በኋላ የቀረበው የጋብቻ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ካገኘ የፍጥምጥም (ቸግ) ቀነ ቀጠሮ በመያዝ ይለያያሉ፡፡ በፍጥምጥም /ቸግ/ዕለትም የምግብና የመጠጥ መስተንግዶ ከተደረገ በኋላ የቃል ማሰሪያ ስነስርዓት ይከናወናል፡፡ በዚሁ ዕለት የልጁ ቤተሰቦች በልጅቷ አካላት ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ዋስ ሲጠሩ የልጅቷ ቤተሰቦችም በአብሮነታቸው ወቅት ንብረት ያለአግባብ ብታባክን ወይም በደል ቢደርስባትም እንኳ ቢሆን ለልጁ ዘመዶች ሳታሳውቅ ቤቷን ጥላ ብትሄድ በሚል ዋስ ይጠራሉ፡፡ አንዳንድ ቤተሰቦች ለልጅቷ የሚሆን አልባሳትና ጌጣጌጥ በፍጥምጥም /ቸግ/ ዕለት ይዘው ሲመጡ አንዳንድ ቤተሰቦች ደግሞ ከፍጥምጥም በኋላ ያመጣሉ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ለጥሎሽ የሚወጣው ወጪ ክፍተኛ የነበረ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በባህላዊ ውሣኔ መሠረት ወጪው መጠነኛ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ሙሽራው ከስርጉ ዕለት ቀደም ብሎ ለሙሽራዋ ልብስና ጌጣጌጥ ይገዛላታል፤በሠርጉ ዕለት ጓደኞቹን ሰብስቦ የተገዛውን ልብስና ጌጣጌጥ በመያዝ ወደ ልጅቷ ቤተሰብ ቤት ይሄዳል :: የሴቷ ቤት የሠርግ ሥርዓት እንደተጠናቀቀ የልጅቷ ቤተሰቦች ዘመዶች ሙሽሮችን እስከ ተወሰነ ርቀት ድረስ አሸኙዋቸውና የሴት አጃቢ ከመደቡላቸው በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ ሙሽራዋ ለጐጅ መውጫ አስፈላጊ የሆኑ ቁሣቁሶችን ይዛ በመሄድ ከአራት ወር እስከ አንድ አመት ድረስ በጫጉላ ቤት ውስጥ ጥሩ ምግብ እየተመገበች ትቆያለች፡፡ በቆይታዋ ወቅትም የሙሽራው ቤተሰቦችና ዘመዶችም መልስ እየጠሩ ይጋብዟቸዋል። በዚህ መልኩ እንክብካቤ እየተደረገላት ከአራት ወር እስከ አንድ አመት ድረስ በጫጉላ ቤት ከቆየች በኋላ ወደ ወላጅ ቤተሰቦቿ ትሄዳለች፡፡
ከወራት በኋላ መልስ ለጠሯት የልጁ ቤተሰቦችና ዘመዶች የተለያዩ አልባሳትንና ቁሣቁሶችን ይዛ በመምጣት ከልጁ ቤተሰቦች ጋር በይፋ ትገናኝ ነበር ። አሁን አሁን መልስ ለጠሯት የልጁ ቤተሰብና ዘመዶች የተለያዩ አልባሳትና ቁሳቁስ ይዞ የመምጣቱ ሁኔታ እየቀረ የመጣበት ሁኔታ የሚስተዋል ሲሆን ከቤተሰቦቿ ቤት ወደ ልጁ ቤተሰቦች ቤት በመምጣት በይፋ የምትገናኝበት ጊዜም እያጠረ መጥቷል። በአብዛኛው በክርስቲያኑ የብሔረሰቡ አባላት ዘንድ ጋብቻ የሚፈፀመው ከመስከረም 5-12 ባሉት ቀናትና በሚያዝያ ወር ውስጥ ሲሆን በሙስሊሙ ደግሞ በአረፋ በዓል ወቅት ነው፡፡ ይህም ከመስቀል፣ከፋሲካና ከአረፋ በዓላት ጋር በተያያዘ ድምቀት ለመስጠትና ከመስተንግዶውም አመቺነቱ ጋር ተያይዞ እንደሆነ ይነገራል፡፡በብሔረሰቡ ሴት ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትወልድ ለአራሷ ለየት ያለ እንክብካቤ የሚደረግላት ሲሆን፤ ማርና ጥሩ ጥሩ ምግቦች ተዘጋጅተው አራሷ ለብርሃን ሳትጋለጥ በመጋረጃ ውስጥ ሆና ትታረሳለች፡፡
የበዓል አከባበር
በብሔረሰቡ የመስቀል፣ የገና፣ የፋሲካ፣ የአረፋ፣ የመውሊድ እና የመሳሰሉት መንፈሳዊ በዓላት ይከበራሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የመስቀልና የአረፋ በዓላት ከሌሎቹ በተለየ መልኩ በድምቀት ይከበራሉ፡፡ የመስቀል በዐል ዝግጅቱ ከነሀሴ 12 ቀን ጀምሮ ዳመራ በየደጁና በየአካባቢው በማቆም ይጀመራል፡፡ ከዚህ ቀን ጀምሮ ወንዶችም ሴቶችም በየፊናቸው ከበዐሉ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ዝግጅቶችን ማከናወን ይጀምራሉ። ሴቶች እንስት የመፋቅና ቅቤ የማሰባሰብ ሥራ ሲሰሩ ወንዶች ደግሞ እንጨት የመፍለጥና ለክብት መግዣ የሚሆን ገንዘብ የማሳባሰብ ሥራ ያከናውናሉ፡፡ ዝግጅቱ በዚህ መልኩ ከተጠናቀቀ በኋላ በዐሉ በየደረጃው የሚከበረው ከመስከረም 13 ቀን ጀምሮ ሲሆን መስከረም 14 ቀን የጐመን ክትፎ ተበልቶ መስከረም 15 የእርድ ሥርዐት ይከናወናል፡፡ ከእርድ ቀን ጀምሮ ጥሬ ስጋ በቅቤ/ጨፉየ/ ፣ጥሬ ስጋ ክትፎ፣ የቅቅል ክትፎና ቅቅል ስጋ በቆጮ እየተበላ በዐሉ እስከሚያበቃበት ቀን ድረስ ይቀጥላል። ከመስከረም 13 ቀን ጀምሮ በዐሉ እስከሚያበቃበት ቀን ድረስ ያሉትቀናትም የተለያዬ ስያሜ አላቸው። በሰባት ቤት ጉራጌ በዓሉ የሚያበቃበት ቀን “አዳብና ተብሎ ሲጠራ በሶዶ ቤተ ጉራጌ ደግሞ ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት 5 ቀን ያለው ጊዜ "አዳብና" ተብሎ ይጠራል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች መስከረም 24 ቀን የበዐሉ ፍፃሜ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቅምት 5 ቀን ይጠናቀቃል፡፡ በአዳብና ዕለትም የብሔረሰቡ አባላት የቅቅል ስጋ ክትፎ በመመገብ ለቀጣዩ አመት መስቀል በሰላም እንዲያደርሳቸው ይመራረቃሉ። የአረፋ በዐልም ከሚከበርበት ጊዜ መለያየትና የእምነቱ ተከታዮች ከሚሰጡት መንፈሳዊ ስያሜ መለያየት በስተቀር በክርስቲያኑ ጉራጌ የሚደረጉት አብዛኞቹ ቅድመና ድህረ የሴትና የወንድ ቅድመና ድህረ ዝግጅቶች ይከናወናሉ፡፡ በዋዜማው ባህላዊ የጐመን ክትፎ የሚበላ ሲሆን ከእርድ ቀን ጀምሮ ጥሬ ስጋ በቅቤ፣ /ጨፉያ/፣የጥሬ ስጋ ክትፎ፣ ቅቅል ስጋና የቅቅል ስጋ ክትፎ በቆጮ እየተበላ እስከ በዐሉ ፍፃሜ ዕለት ድረስ በየደረጃው በድምቀት ይከበራል፡፡ በብሔረሰቡ ለአዛውንቶች የሚሰጠው ክብርና እንክብካቤ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሣ የሽማግሌዎችና በዕድሜ የገፉ እናቶች ምርቃት ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ታሪካዊ ክንዋኔዎችንና የወቅቶችን መፈራረቅ መሠረት ያደረገ የራሳቸው የሆነ የቀን፣ የወራት፤የወቅቶችና የዘመን አቆጣጠር አላቸው፡፡
ባህላዊ የቤት አሰራር
በብሔረሰቡ ባህላዊ ቤት ለመስራት ሲታሰብ የተለያዩ የእንጨት ዓይነቶችን የማሰባሰብና ለቤት መስሪያ የተመረጠው ቦታ የመደልደል ሥራ በቅድሚያ ይከናወናል፡፡ እነዚህ ሂደቶች እንደተጠናቀቁ የአካባቢው ሰዎች በባህላዊ አናፂ እየተመሩ በየደረጃው መከናወን ያለባቸውን ሥራዎች ያከናውናሉ፡፡ የጣሪያና የግድግዳ ማገሮችን በእንስት ገመድ ሲያስሩ የግድግዳው ማገር ጥንካሬ እንዲኖረውም ሀረግን ይጠቀማሉ፡፡ ግደግዳውና ጣሪያው ተሠርቶ እንደተጠናቀቀ በአካባቢው እንደሚገኘው የክዳን ዓይነት በሣር፤ በሰንበሌጥ፣ በስንደዶ፣ በገብስ ወይም በስንዴ አገዳ ይከደናል፡፡
ለቤት መስሪያነት የሚውሉ የእንጨት ዓይነቶችም ከቦታ ቦታ ስለሚለያዩ ምርጊቱም በዚያው መጠን ይለያያል። በቀርከሃ ማገር የተማገረ ቤት ከሆነ የውስጠኛው ክፍል በእበት ተመርጐ መሀሉ ላይ ዙሪያው በነጭ ኖራ ይቀባል። በአጠና ወይም በጨፈቃ የተማገረ ከሆነ ደግሞ የውስጠኛው፣ ወይም ውስጡና ውጪው በጭቃ ሲመረግ በአንዳንድ አካባቢዎች በቀይ ወይም በነጭ የአፈር ቀለም ያስውቡታል። ቤቱ ተሰርቶ ከተጠናቀቀ ለተለያዩ አገልግሎቶች በሚውል መልኩ ከተከፋፈለ በኋላ የተለያዩ ባህላዊ የመገልገያ ቁሳቁሶች በግድግዳ ላይ ይስቀላሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች አንድ አባወራ የተለያየ መጠን ያላቸውና ለተለያዩ አገልግሎቶች ባህላዊ ቤቶች ሊኖሩት ይችላል፡፡ የሚውሉ እስከ ሶስት ብሔረሰቡ ከቃጫ ከገመድ ከብረታ ብረትና ከእንጨት የተለያዩ ቁሳቁሶችና ከእንስት ተረፈ ምርቶች ደግሞ ለመኝታና ለወለል ምንጣፍነት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ሰማዘጋጀት ይጠቀማል። ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውም በአብዛኛው ተመሳሳይነት ያላቸው ሲሆኑ በአንዳንድ ቤተ ጉራጌዎች ከስያሜና ከመሣሪያዎች አዲያ መጠነኛ ልዩነቶች እንዳላቸው ይነገራል፡፡ እነዚህ የሙዚቃ መሣሪያዎች የትንፋሽ የምትና የክር ተብለው በሦስት ይከፈላሉ፡፡ ከትንፋሽ ዋሽንት (ቱቲና) መለከት፣ ጡሩምባ፣ ከምት ከበሮ (አንድር)፣ ድቤ (ጀበርን) ክራር እና አታሞ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የብሔረሰቡ አባላት እነዚህን የሙዚቃ መሣሪያዎች በመጠቀም በሠርግ በእርሻ በክብረ በዓላት ወቅትና ጀግኖችን ለማወደስ የተለያዩ ባህላዊ ዘፈኖችንና ጭፈራዎችን ያከናውናሉ፡፡
ባህላዊ ምግብ አዘገጃጀት
የጉራጌ ብሔረሰብ የእንሰት ውጤት የሆነ-ት ቆጮ፣ቡላ እና አምቾ በተለያየ መልኩ በማዘጋጀት በባህላዊ ምግብነት ይጠቀማል፡፡ የእንሰሳት ተዋፅኦችንና አትክልቶችም በተለያየ መልኩ ከተዘጋጁ በኋላ ለማባያነት ይውላሉ፡፡ ከሥጋ፣ ከጕመን፣ ከአይብና ከቅቤ ከሚዘጋጁት ማባያዎች መካከል የሥጋና የጐመን ክትፎ፣ 'ፍንታፍንቶ ዝማሞጀት" “ኧቆት"፣ "ቆቆስየ” ፣ “ጨፉየ”ና ሌሎችም ተጠቃሾች ናቸው። ከነዚህም ውስጥ ክትፎ በቆጮ የብሔረሰቡ አይነተኛ የባህል ምግብ መሆኑ በአብዛኛጡ የሀገራችን ህዝብ ዘንድ ይታወቃል። እንዲሁም የተመረጡ የእንሰት ዓይነቶችን አምቾ ከመደበኛ ምግብነት በተጨማሪ ለስብራት ጥገናና ለሌሎች የበሽታ ዓይነቶች ለመድሀኒትነት ይጠቀሙበታል፡፡ ሌሎች የእህል ዓይነቶችንም በተለያየ መልኩ በማዘጋጀት ይጠቀማሉ፡፡
ባህላዊ አለባበስ
በነባር ባህሉ የጉራጌ ብሔረሰብ ከቆዳ፣ ከጥጥ፤ ክሱፍ እና ከሐር የተሰሩ አልባሳትን በመስጠት ይጠቀምባቸው ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ አልባሳትና መጠሪያቸው በአሁኑ ወቅት በአገልግሎት የሌሉና ለእይታም እንኳን የማይገኙ ሆነዋል። አዝማቾች /ንጉሦች/ ካባ ይደርባ ጐንደር /አምባር/ በእጃቸው ያጠልቃሉ፡፡
የሐዘንና የለቅሶ ሥርዓት
በብሔረሰቡ የለቅሶና የሀዘን ሥርዓት በዕድሜ ደረጃ ይለያያል፡፡ ወጣቶች፣ ጐልማሶችና ትልልቅ ሰዎች ሲሞቱ ሩቅ ያለ ዘመድ እስከሚመጣ ድረስ ሳይቀበርሊቆይ ይችላል፡፡ ታላላቅ ሰዎች ሲሞቱ ከመደበኛው የለቅሶ ሥርዓት በተጨማሪ የሟቹን/የሟቿን ጀግንነት፣ ለጋሽነት፣ ታታሪነት ባለሙያነትና እንግዳ ተቀባይነትን፣ አስታራቂነት፣ታጋሽነት አስተዋይነት እና ሌሎችም የሚያወሱ ነባር ግጥሞች እየተደረደሩ ይለቀሳል፡፡ ይህ ዓይነቱ የለቅሶ ሥርዓት የሟቹን ማንነት ከመግለፁም በተጨማሪ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ የብሔረሰቡ አባላት እርስ በርሳቸው እንዲማማሩ፣ እንደሚያግዝ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል በብሔረሰቡ ውስጥ የጐሣ መሪ /አዝማች/ ሲሞት ደግሞ በአንድ በኩል እየተለቀሰ በሌላ በኩል እየተጨፈረ አዋቂዎች ከበሮ እየመቱ በሰልፍ የለቅሶ ሥርዓት ያደርጋሉ፡፡ ከለቅሶው ሥርዓት ጐን ለጐንም ሟቹ ሣይቀበር የሟቹ የበኩር ልጅ የሟች አባቱን አንባር /ጐንደር/ በመውረስ ሥልጣን ይረከባል፡፡