Skip to main content

ጠንባሮ

                        የጠምባሮ ብሔረሰብ
የጠምባሮ ብሔረሰብ ከሚገኙት ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ሲሆን በዋናነት በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ይገኛል።ልዩ ወረዳው በ1 የከተማ አስተዳደር፣ በ18 የገጠርና በ7 ከተማ ቀበሌዎችማ የተዋቀረ ነው። የወረዳው ዋና ከተማ ሙዱላ ነዉ፡፡የህዝብ ቁጥሩ መ/ኢ/ክ ፕላን እና ልማት ቢሮ 2017 ዓ.ም ፕሮጄክሽን መሠረት የልዩ ወረዳ ህዝብ ብዛት ወንድ 84,635 ፣ሴት 89,120 ድምር 173,755
                             ቋንቋ
የጠምባሮ ብሔረሰብ የአፍ መፍቻ ቋንቋ "ጠምባርሳ” ነው፡፡ ቋንቋው ከኩሽ የቋንቋ ቤተሰብ እንደሚመደብ የስነ ልሳን መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን ከከምባትኛ፣ ከአላብኛ፤ ከሀዲይኛ፣ ቀቤንኛ፣ ሲዳምኛ እና ጌዲኦፋ ቋንቋዎች ጋር የቀረበ ግንኙነት ያለው ነው፡፡በ2003 ዓ.ም የብሔረሰቡ ባህልና ታሪክ በቀድሞዉ ክልል በብሔረሰቦች ምክር ቤት እና በሀዋሳ ዩኒቬርሲቲ ተጠንቶ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ ተደርጓል፡፡
                የብሔረሰቡ ታሪካዊ አመጣጥ
ከብሔረሰቡ የዕድሜ ባለፀጋ ታሪክ አዋቂዎች በተገኘው መረጃ መሰረት የጠምባሮ ብሔረሰብ ከጥንታዊው ሀዲያ-ሲዳማ ነገድ እንደሆነ ይነገራል። የብሔረሰቡ ቀደምት ህዝቦች ከአረብ ሀገር የቀይ ባህር ዳርቻ የሆነችውን "ዘይላ" ወደብን ተሻግረው ወደ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ በአገሪቱ በስተምስራቅ የሐረሪ ህዝቦች በሚኖሩበት አካባቢ ለተወሰነ ጊዜያት እንደኖሩ፤ ከጥቂት ቆይታ በኋላም በሐረርጌ ጨርጨር፣ በአርሲ ዲሁም በአርሲና በባሌ አዋሳኝ ስፍራዎች አካባቢ ሠፍረዉና ቆይታካደረጉ በኋላ በባሌ በኩል ወደ ሲዳማ ደጋማው ምድር በርካታ ዓመታት ዘልቀው በመኖር ከሲዳማ ቡሼ ዘር ከሆኑት መካከል ሰባት ወንድማማቾችን የያዘ ቡድን ወደ ዛራዋ ጠምባሮ ምድር በ16ኛው ክ/ዘመን ገደማ እንደመጡ ይነገራል፡፡
                                               ባህላዊ አስተዳደር
የጠምባሮ ብሔረሰብ ባሣለፋቸው ታሪካዊ ሂደቶች የፈጠራቸው የራሱ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ያለው ነው፡፡ በብሔረሰቡ ውስጥ ከጐሣ መሪዎች ጀምሮ እስከ የበላይ አስተዳደር መሪዎች ድረስ አራት የባህላዊ አስተዳደር የሥልጣን ደረጃዎች እርከኖች/ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የጐሣ መጋባ፣ ባሌ /ላሂ/ ወማ፣ ኮሮፍራ /ጋዲ ወደ/እና የቶቤ ሸንጐ ወይም ምክር ቤት በመባል ይታወቃሉ፡፡
የጐሣ መጋባ በባህላዊ አስተዳደሩ መዋቅር ዝቅተኛና የመጨረሻ የስልጣን እርከን ነው። የጐሣ መጋባ የአንድ የጐሣ አስተዳደራዊ ተግባራትን፣ ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶችን፣ የፍትህ ጉዳዮችን ያያል፣ ይመረምራል፣ ይመራል፡፡ የመጋባ ምርጫ መመዘኛ በዕድሜ ከሌሎች አባላት የተሻለና የመምራት ብቃት ያለው እንዲሆን ይፈለጋል፡፡ የጐሣ መጋባ የተለያዩ የማህበረሰቡን ችግሮች በሚፈታበት ወቅት “ወንበራ” የሚባሉ ረዳቶች ይኖሩታል፡፡ በሥሩ “ቤጣባ" የሚባል ፀጥታ አስከባሪ ኃይል ያለው በ'ወማ" እየታዘዘ ማናቸውንም ፀጥታ የማስከበር ተግባርን ያከናውናል። “ላሂ ወማ" ስያሜውን ያገኘው ጥንት የብሔረሰቡ ተወላጆች ይዘውት ከመጡትና ዛሬም “የሥልጣን ምልክት' አድርገው ከሚጠቀሙበት ቀለበት ነው፡፡
ይህ የባህላዊ አስተዳደር ንግስና ምልክት ከወማ ሥልጣን ርክክብ ጋር የሚተላለፍ ነው። “ለሐ" የሚባለው ባህላዊ የሥልጣን ምልክት የሚቀመጠው በማርና በትኩስ ወተት እየታጠበ በመሆነ የማብረቅረቅ ባህሪይ አለው፡፡ ይህን የአስተዳደር ደረጃ አንድ “ወማ˚ ሲረከብ ከንግስ ምልክቱ ቀለበት ወይም አምባር በተጨማሪ ሌሎች መተዳደሪያ የሚሆኑ ስጦታዎች ጭምር ይሰጡታል፡፡ የሥልጣን ርክክቡ ሥርዓት ምርጫው "በቶቤ ሸንጐ" /በምክር ቤቱ/ ስብሰባ በኮሮፍራ መሪነት የሚወሰን ሲሆን ሥነ ሥርዓቱ የሚካሄድበት ሥፍራ “ቱጳ” በብሔረሰቡ ዘንድ ሹመት የሚሰጥበት ወይም የሚነሣበት ቅዱስ ሥፍራ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ቦታው ከሙዱላ ከተማ በስተምሥራቅ ሁለት ኪ.ሜ ርቀት ላይ “ቦሄ በምትባል ቀበሌ ውስጥ ይገኛል፡፡ ለእርቅ፣ ለምክክር፣ በዓል ለማክበር... ወዘተ/ በሙዱላ ከተማ የሚገኘውን ታሪካዊ የደገሌ ዋርካን ይጠቀማሉ ።
የ "ጠማ" ሥልጣን ለእያንዳንዱ ጐሣ ተራ በተራ የሚተላለፍ እንጂ የአንድ ጐሣ የዘር ሀረግን ተከትሎ ከምርጫ ውጪ የሚፈፀም አይደለም። ለዚህ ቦታ የሚመረጥ ሰው ከውርስ ሚስት ያልተወለደ፣ ችሎታው ተመዝኖ፣ ብቃቱ ተጠንቶና ተገምቶ እንጂ እንዲሁ በደፈናው ስልጣኑ አይሰጥም። በዚህ መልኩ የተመረጠው አካል ሥልጣኑን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ ባህላዊ በዓል ይከበርለታል፡፡ የወማ የሥልጣን ዘመን ከ 2-4 ዓመት ሲሆን በአንዳንድ አጋጣሚዎች ከ 4-10 ዓመት አገልግሎት ይሰጡ እንደነበሩ ይነገራል። "ወማ" ሥልጣኑን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ወደ ገበያ፣ ለቅሶ፣... ወዘተ አስፈላጊ ባልሆነ ቦታና ጊዜ እንዲሄድ አይፈቀድለትም፡፡ የስልጣን ርክክብ የሚፈፀመውን የሚፀድቀው ከህብረተሰቡ የተመረጡ ሴቶች በተገኙበት እና ስልጣኑ የሰላም፣ የብልጽግና የጥጋብ እንዲሆን ከመረቁ ብቻ ነው፡፡
የኮሮፍራ /ጋዲ ወማ/ ሥልጣን የብሔረሰቡ መንፈሣዊና ሥነ ልቦናዊ በሆኑ እምነቶች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ኮሮፍራ የሚመረጠው በቶቤ ሸንጐ /በምክር ቤቱ/ሆኖ የምርጫ መመዘኛው ዓለማዊ ስሜቶችንና ፍላጐቶችን የማያንፀባርቅ አዛውንት እንደሆነ ሲታመን ነው፡፡ የኮሮፍራ ሥልጣን አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀርየዕድሜ ልክ ሥልጣን ነው፡፡ ሥልጣን ሲረከብ በሚዘጋጀው ባህላዊ ሥነ ሥርዓት ላይ መሲና ላም ታርዳ ቃለ መሀላ ባላና ሣር ተይዞ ይፈዕማል፡፡ አንደበቱ፣ ምኞቱና አቋሙ የመውላ /የ7ቱ ጐሣዎች አባት/ ስለሆነ የመረቀው ወይም የረገመው ጽኑ እነደሆነ ይታመናል።
ኮሮፍራ የባህላዊ እምነት ሥርዓቶችን የመምራት ኃላፊነት አለው፡፡ በብሔረሰቡ “ቡሻሻ” ማለት የኮሮፍራ የማዕረግ መጠሪያ ሲሆን ትርጉሙ የተከበረ፣ የተወደደ የብሔረሰቡ ታላቅ አዛውንት እንደማለት ነው፡፡ በጠምባሮ ብሔረሰብ ታሪክ እስካሁን 13 ኮሮፎራዎች ተፈራርቀዋል፡፡ የቶቤ ሸንጐ የብሔረሰቡ ከፍተኛ ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ሽንጐ የብሔረሰቡን ባህላዊ መሪዎች የመምረጥ፣ ህግ የማውጣት፣ ወማና ኮሮፍራ የማስመረጥና የመሻር፣ ሥልጣንና ኃላፊነት ያለው ሲሆን የሸንጐው ምርጫ የሚከናወነው አግባብነት ካላቸው ጐሣዎች ነው፡፡ ቶቤ ሸንጐ ወማ በሥልጣን ዘመኑ ጥፋት ከፈፀመ ውሣኔ እስከሚሰጥ ወይም ሌላ እስከሚተካ ሥልጣኑ በኮሮፍራ እጅ ተይዞ እንዲቆይ ይደርጋል፡፡
በብሔረሰቡ ባህልና ልማድ እያንዳንዱ ሰው ትክክለኛ ፍትህ የማግኘት መብት ከፈጣሪ እንደተሰጠው ይቆጠራል፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ በተለያየ ደረጃ የሚከሰቱትን ግጭቶች የሚፈታበት የራሱ የሆነ ባህላዊ ሥርዓትና ሥልት አለው። እነዚህ ስርዓቶች ተግባራዊ የሚደረጉት ህዝቡ በባህላዊ አስተዳደሩ ሥርዓት በመረጣቸው ባህላዊ መሪዎች እንደሆነ ይነገራል፡፡
በመሆኑም ከመውላ የዘመድ ጐሣዎች መካከል ኮሮፍራ፤ ግብ እና ወማ ተመርጠው ሁሉንም የጠምባሮ ህዝብ የመምራትና የመዳኘት ሥልጣን አለው። በእነዚህ አካላት ተግባራዊ የሚደረገው የዳኝነት ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ስብዕናንና የተፈጥሮ መብትን መሠረት ያደረገና ፍትሀዊ አመራርን የተከተለ ነበር :: የችግር አፈታት ሂደቱ እንደየችግሮቹ ደረጃ ከመጨረሻ የባህላዊ አስተዳደር ጀምሮ እስከ ትልቁ ሥልጣን ድረስ ሊመጣ ይችላል፡፡ የዚሁ መሠረት የመጀመሪያ አቤቱታ ለንዑስ ጐy መሪ ይቀርባል።


በብሔረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ግጭቶች የሚባሉት እንደ ነፍስ ግድያና የጐሣ የእርስ በርስ ግጭቶች ሲሆኑ፤ የነፍስ ግድያ ከተፈፀመ የእርስ በርስ በቀልና ጥቃት እንዳይፈፀም የገዳይ ወገን በአፋጣኝ ውሎ ማያድር ጥፋት በእጃችን ወዚ˘ እያሉ ይቀርባሉ፡፡ በብሔረሰቡ ቋንቋ “ወዚ" ማለት "ይቅር በሉኝ፣ ታደጉኝ እንደማለት ነው። የገዳይ ወገኖች "ወዚ" እያሉ ወማ ዘንድ ሲቀርቡ ፊታቸውን ጥላሸት ይቀባሉ፣ በልብስ ምትክ ቅጠል ይለብሣሉ /ያገለድማሉ፤ ድንጋይ በጭንቅላታቸው ይሽከማሉ፤ በሌሎች እንዳይታዩ ጉዞአቸውን ሌሊት ያደርጋሉ፡፡ ይህ የሚያደርጉት ወንድማቸው በመሞቱ ማዘናቸውን ለመግለፅ ነው፡፡
ወማ እና ኮሮፍራ እጅ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሟች ወገኖች ዘንድ በቀል የመፈፀም ስሜት አይኖርም፡፡ ጉዳዩ ውሳኔ እስከሚያገኝ ድረስ ወገኖቹ ገበያ ወይንም አደባባይእንዳይወጡ ከታገዱ በኋላ ቅራኔው ውሎ ሳያድር በቶሎ እንዲፈታ ይደረጋል፡፡ በመጨረሻም ያጠፋው ወገን /በዳይ/ “ጉማ” ወይንም ካሣ እንዲከፍል ይወስናል፤ የተበዳይ ወገንም ይቅር ለእግዜር በማለት በመካከላቸው እርቅ እንዲወርድ ያደረጋል።
                                                 ባህላዊ እሴቶች
                                                  የጋብቻ ሥርዓት
በጠምባሮ ብሔረሰብ ተግባራዊ የሚደረጉ አራት ባህላዊ የጋብቻ ዓይነቶች አሉ፡፡ እነዚህም በቤተሰብ በስምምነት የሚፈፀም ጋብቻ /ቆርሲሻ/ ፤ አባብሎ የመውሰድ ጋብቻ /ላቡኡ/ ላቦ I የጠለፋ ጋብቻ ሔሩ /ሚዲ/ እና የውርስ ጋብቻ /ራጋ/በመባል ይታወቃሉ፡፡ በቆርሲሻ ጋብቻ የወንዱ ወላጅ አባት ልጃቸው ማንን ማግባት እንዳለበት ምርጫውን ከወሰነ በኋላ ሁለት ያህል ታዋቂ ሽማግሌዎችን ይዞ ወደ ሴቷ ወላጆች ቤት ይሄዳል፡፡ ሽማግሌ ወደ ልጅቱ ቤተሰቦች ለመላክ ወርና ቀን ተመርጦ ሲሆን ከወራት የካቲት ከቀናት ደግሞ ሰኞ ተመራጭ አይደሉም፡፡ የሴቷን ቤተሰቦች /ወላጆች/ ፈቃደኝነት ወይም ስምምነት ለመጠየቅ የሚላኩ ሽማግሌዎች አቤታቸው ተነስተው ጉዞ በሚጀምሩበት ጊዜ የተለያዩ ባህላዊ እምነቶችን መሠረት እያደረጉ ነው፡፡ የበጐ ነገር መገለጫዎች ናቸው ባሏቸው ምልክቶች እየተመሩ ይፈጽማሉ። ሁኔታዎች ተሳክተው ያለምንም ሣንካ ወደ ልጅቱ ቤት የደረሱ ሽማግሌዎች ሣይፈቀድላቸው ወደ ቤት አይገቡም፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ወደ ቤት እንዲገቡ ይደረጋል። ሽማግሌዎቹ ከገቡ በኋላ በሴቷ ወላጆች ፊት ቆመው የመጡበትን ጉዳይ “ልጅዎ እና ልጃችን ይውለዱ" በማለት ጥያቄያቸውን ያቀርባሉ፡፡ ለቀረበው ጥያቄ የሴተ ወገኖች ፈቃደኝነት እንደታወቀ ለቃል ማሠሪያ ቀን ቀጠሮ ይወስዳሉ፡፡ የተወሰነውን ቀነ ቀጠሮ በተመለከተ የእሽታም ሆነ የእመቢታ መልስ ወዲያውኑ አይሠጣቸውም:: ስለ ልጁና ቤተሰቦቹ በሴቷ ወገኖች በኩል የሚጠነ ነገሮች ይቀጥላሉ፡፡ በተለይ የዘር ሐረግ የዝምድና ግንኙነት መኖር ያለመኖርየማጣራት ሂደት ይቀጥላል፡፡ ይህም እስከሚከናወን ጊዜ ይሰጠንና የመጨረሻ ውሣኔውን በአገናኝ ሽማግሌ በኩል ተከታተሉ ይባልና ይሸኛሉ፡፡
በሴቷ ወገኖች የሚደረገው የማጣራት ሂደት እንደተጠናቀቀ የቃል ማሠሪያው ቀን ይፋ ይደረጋል፡፡ በዚህም የሴቷ ቤተሰቦች ፈቃደኝነት ይረጋገጣል፡፡ በቃል ማሠሪያ ዕለት ከወንዱ ቤተሰቦች ለሴቷ ወገኖች የሚስጠው የመጀመሪያው የስጦታ /ጥሎሽ/“አፌ ፋን በሪ" ወይም "አፍ መፍቻ” በመባል ይታወቃል፡፡ በቃል ማሠሪያ ወቅትም ሆነ በሠርግ ጊዜ ለልጅቷ ቤተሰቦች የሚቀርበው የጥሎሽ ክፍያ በወንዱ ቤተሰብ ሀብት መጠን ይወሰናል፡፡ የሴቷ ወገኖች የሚወስዱትን መጠን ያህል ስጦታ በሠርጉ ወቅት ከልጅቱ ጋር መልሶ መስጠት ስለሚኖር ሲወስዱ ያንን ሁሉ ከግምት ያስገባሉ። በዚሁ የጥሎሽ ቀን ለልጅቱ የአንገት ማህተም በብሔረሰቡ ቋንቋ “ሶፋ” ወይም “ጃናቲ” ወይም “ዩሻ” ይደረግላታል፡፡ በእጅዋ ላይ ደግሞ አምባር መሰል /"ወጫታ”/ ይታሠርላታል፡፡ ለአባት የብር ቀለበት፣ ቡልኮ፣ ማር፣ ኮርማ በሬ፣ ወይፈን፣ የክብር መቀነት /ደባሊ ጠጠባ/ የሚስጥ ሲሆን ለእናት ጊደር፣ መቀነት፤ ለአጐት ፈረስ በስጦታ ማቅረብ የቆየ ባህላዊ ልማድ ነው፡፡
የቃል ማሠሪያው ሥነ ሥርዓት ከተጠናቀቀና ሁለተኛው የጥሎሽ አሰጣጥ እንዳበቃ የሠርግ ቀን ይወስናል፡፡ ይህም ቢያንስ ከ2-3 ወራት ጊዜ እንደሚቆይ ይነገራል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት በሁለቱም ወገኖች የሠርግ ዝግጅትና የስጦታ ዕቃዎችን ማሰባሰብ ይጀመራል፡፡ በጠምባሮ ባህል ሴት ልጅ ከጋብቻዋ ዕለት በፊት መገረዝ ስላለባት የሠርግ ቀነ ቀጠሮ ከተያዘ በኋላ በቤተሰቦቿ ቤት ትገረዛለች፡፡ በባህሉ ያልተገረዘች ልጃገረድ አትሰጥም፡፡ ይህ ባህላዊ ሥርዓት አሁንም ያለ ነው፡፡
ሙሽራው ወይንም የሙሽራው ወንድም እዚያው እንደደረሱና ከቤቱ መግቢያ ላይሆነው የተለያየ ሠላምታ በጭፈራ መልክ ካቀረቡ በኋላ ሲፈቀድላቸው ወደ ቤት ይገባሉ፤ አዚያም ሙሽሪት ወደምትገኝበት ስፍራ ሄደው ከቤተሰቦቿ ያገኘችውን የተለያዩ ስጦታዎች ቆጥረው በእልልታና በጭፈራ ይረከባሉ፡፡ ለሙሽራዋ ለጐጆ መውጫ ጊደር፣ ወይፈንና፣ ቡልኮ፣ ፈረስ፣ በቅሎ… ወዘተ ይሰጣሉ፡፡ በባህሉ መሠረት ሴቷ ወደ አዲሰ የትዳር ቤቲ ስትሄድ የሚሰጣት “ቅቤ” ሁለት ዓይነት ስያሜ አለው፡፡ የመጀመሪያው በቋንቋው “ዙሪቡሮ" የሚባል ሲሆን፣ አገልግሎቱ ለምግብነት የሚሆን ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ "ሀንቃሮ ቡሮጀ ሲባል ሙሽሪት ወደ ቤት ስትገባ አማትዋ በር ላይ ቆማ አቅፋ ስለምትቀበላት በዚያን ጊዜ የምትሰጠው ስጦታ ነዉ፡፡ ሙሽሪት ከቤተሰቦቿ ከመውጣቷ በፊት ዘመዶቿ ቁርበት አንጥፈው፤ መቀነታቸውን ፈትተው ይመርቋታል፡፡ እናቶች መከቀነታቸውን የሚፈቱበት ምክንያት ልጃቸው ወላድ እንድትሆንላቸው ያላቸውን መልካም ምኞት ለመግለፅ ነው፡፡
ከወንዱ ቤት የመጣው ሠርገኛ ወደ ሴቷ ቤተሰቦች ቤት ይገባና በስምንት ዋንጫ የተሞላ መጠጥ /በብሔረሰቡ “ዊማ ለሙሽሪት ወገን ሽማግሌዎች ቀርቦላቸው ሁለቱም ወገኖች እየተለዋወጡ፣ እየተቀባበሉ ይመራረቃሉ፡፡ በመጨረሻም ሠርገኛው ሙሽሪትን እንደተቀበለ ሚዜው በጀርባው ተሸክሞ ከቤት ያስወጣታል፡፡ ከዚያም መጀመሪያ ፈረስ /ባዝራ/ ላይ አስቀምጠው፤ ጉዞ ይጀመራል፡፡ በፈረስ ላይበመጀመሪያ የሚያስቀምጧት ወላድ እንድትሆን ምኞታቸውን ለመግለፅ ነው፡፡ ሙሽሪት ከቤቷ ወጥታ ሙሽራው ቤት እስከምትደርስ ድረስ ፊቷ በነጠላ ይሸፈናል። ሠርገኛው ሙሽራው ቤት እንደደረሰ ሙሽሪት የጊደር ወይንም የላም ጭራ ይዛ ወደ ቤት እንድታመራ ይደረጋል፡፡ ይህም የሚደረገው ሙሽሪት ወላድ እንድትሆን ምኞትን መግለጫ ሲሆን ጊደሯም ስጦታዋ ልትሆን ትችላለች። ወደ ቤት ከመግባትዋ በፊት በግ ታርዶ ደሙን እየረገጠች እንድትገባ ይደረጋል፡፡ ሙሽሪት እቤት ውስጥ እንደገባችም በአማቷ ጭን ላይ እርጥብ ሣር ወይንም ቅጠል ተደርጐላት ትቀመጥና ባህላዊ ሥርዓት ይካሄዳል፡፡ በቅቤ የታሸ የገብስ ቆሎ /ቡራቶ/ግስሃ ይቀርባል፡፡ የሙሽራው እህት ጫጉላ ቤት ገብታ የሙሽሪትን መቀነት ትፈታለች፤ ልብሷን የማወላለቅ፣ ከሙሽራው ጋር እንዲገናኙ የማድረግ፣ የማለማመድ ኃላፊነት አለባት፡፡ በማግስቱ ጥቁር በግ ታርዶ “ሉጋኖ” የሚባል ባህላዊ ደንብ ይፈፀማል፡፡ የታረደውን በግ ሥጋ ቤተሰብ አይመገብም፡፡
በመልስ ዕለት እናት ማር ወይንም ትኩስ ወተት በዋንጫ አስይዛ በመሄድ በሙሽሮች እግር ላይ ታፈሳለች፡፡ ይህ ክሆነ በኋላ ፊታቸውን ተሸፋፍነው ውጪ እንዲቆዩ የተደረጉ ሚዜዎች፣ ሙሽራዎችና ሠርገኞች ፊታቸውን ገልጠው ወደ ቤት እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ እናት የሚጠጣ ነገር በእጅዋ መዳፍ ላይ እያፈሰሰች፣ ሁለቱንም እያቀመሰች ትመርቃለች፡፡ በዚህ የመልስ /ኪፋ/ ቀን ቀደም ሲል ያልተከፈለ ጥሎሽ ካለ እንድ ላይ ይፈፀማል፡፡
የማባበል ጋብቻ /ላቡዑ/ላቦ/


ሁለተኛው የጋብቻ ዓይነት አባብሎ የመውሰድ ጋብቻ ወይንም በብሔረሰቡ ቋንቋ "ላቡኡ” ወይንም “ላቦ" በመባል ይታወቃል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጋብቻ በሶስተኛ ወገን በተለይ በወንዱ የቅርብ ዘመድ ወይንም የአካባቢ ሴት ልጆች አማካይነት የሚፈፀም ነው፡፡ ይህ ጋብቻ አንዳንድ ጊዜ በቤተሰብ እውቅና የሚከስት ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ ያለቤተሰብ እውቅና በድብቅ ይፈፀማል፡፡ በቤተሰብ እውቅና የሚፈፀም የማባበል ጋብቻ ከተጫጩ በኋላ ለሠርግ ከተያዘው ቀነ ቀጠሮ በፊት ሠርግ ከመደገስና ወጪን ከማብዛት ልጃቸውን በሶስተኛ ወገን አማካይነት በማባበል በምክክር እንድትወስድ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ፡፡ ሌላው የዚህ ጋብቻ መከሰቻ ወንዱ ሴቷን ሲወድና ለማግባት ግን አቅሙ የማይፈቅድ ሆኖ ከተገኘ ወይንም ልጅቱ ለሌላ ሰው የታጨች ከሆነ በጉልበት በሶስተኛ ወገን አማካይነት በማባበል ከመግለጽ በፊት ስለ ልጁ ቁመና፣ ባህሪይ እና የማስተዳደር አቅም በቂ መረጃ ማግኘት ስለምትፈልግ ልጁን አይታ በቁመናው ከተማረከች ስምምነትዋን ትገልጽና ትሄዳለች፡፡
                                                   የጠለፋ ጋብቻ /ሄሩ/
ለጠለፋ ምክንያቶች የወንዱ በሀብትና በወገን መመካት፣ የልጅቱ ቤተሰቦች ጋብቻ ጠያቂውን ቤተሰብ በመናቅ ፈቃደኛ አለመሆን፣ የሁለቱ ወገኖች በጐሣ/በዘር/አለመመጣጠን ከሀብታም ቤት /ጐሣ/ በጋብቻ ለመጠጋት /ለመዛመድ/ ማሰብ፣ ከጥሎሽ እና ከሠርግ ወጪ ለመዳን መፈለግ ናቸው። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ጋብቻ ከፍተኛ አደጋና ጉዳት ሊያስከትል፣ በማህበረሰቡ ዘንድ የጐሣ ግጭትን A35 5G ይችላል፡፡ እንዲሁም የተጠለፈች ሴት ልጅ በትዳር ዓለም ዉስጥ ከዉጪም ሆነ በቤተሰቦቿ ዘንድ የሚኖራት ዝቅተኛ ግምት ሊሆን ስለሚችል ሞራሏ የተጐዳ ይሆናል፤ በመሆኑም የጠለፋ ጋብቻው ብዙውን ጊዜ የተወገዘ ነው፡፡
                                                  የውርስ ጋብቻ /ረጌ/
የውርስ ጋብቻ ባሏ የሞተባት ሴት ከሌላ ጐሣ የሆነ ወንድ ብታገባ ችግር ያስከትላል ተብሎ ስለሚታመን የሟችን ሚስት የሟች ታናሽ ወንድም እንዲያገባ ይደረጋል፡፡ የጋብቻው ዋና ዓላማ የሟች ልጆችንና ሀብትን በቤተ ዘመድ ለመንከባከብና ለመጠበቅ ነው፡፡ በመሆኑም እንዲህ ዓይነቱ ጋብቻ የሚፈፀመው በሟች ሚስትና ቤተሰቦች ምክክርና የቤተ ዘመድ ጉባኤ ውሣኔ መሠረት ነው፡፡ ውሣኔውን የሟች ወንድም አምኖ የመቀበልም ሆነ ያለመቀበል መብቱ የተጠበቀ ሲሆን የሟች ሚስት ግን ከፍላጐቷ ውጪም ቢሆንም ውሣኔውን ለመፈፀም ባህላዊ ጫና ይደረግባታል፡፡
በብሔረሰቡ ባህል አንዲት ሴት የመጀመሪያ ልጅዋን የምትወልደው ወደ ቤተሰቦቿ ዘንድ ቀደም ብላ በመሄድ ነው፡፡ እንደወለደች ባል ከእናቱ ወይንም ከእህቶቹ ጋርሙክት፣ ማርና ቅቤ በመያዝ ሄዶ ጠይቆ፣ባህላዊ ምርቃት ሰጥቶ ይመለሣል፡፡ እሷም የአራስ ጊዜዋ ሲያበቃና ህፃነ-ም ጠንከር ሲል የእሱ ቤተሰቦች ሄደው ወደ ቤቷ ያመጧታል፡፡ ስትመለስም የተለያዩ ስጦታዎችና የምግብ ዓይነቶች ተዘጋጅተው ይሰጧታል፡፡ ቤቷ እንደደረሰችም ከባሏ ቤተሰቦች ስጦታ ለመቀበል /በተለይ ከብት፤ መሬት፣ ፈረስ/ ስትል “ህፃነ ጡት አልጠባ አለ" የሚል ስበብ /ምክንያት/ታቀርባለች፤ አራሷ ወደ ቤቷ ስትገባ የባል እናት ባህላዊ መጠጥ በዋንጫ እያቀረበች ትመርቃታለች፤ ፀጉሯንም ቅቤ ይቀባሉ፤ የተለያዩ ስጦታዎችንም ይሰጧታል፡፡

                                       ባህላዊ በዓላትና የአከባበር ሥርዓት
በብሔረሰቡ ዘንድ በስፋት ከሚከበሩ በዓላት መካከከል አንዱና ዋነኛው ማሣላ" ወይንም የመስቀል በዓል ነው፡፡ ማሣላ ብሔረሰቡ ዘንድ እንደ ዘመን መለወጫ ሆኖ ይከበራል፡፡ የመስከል በዓል ጨረቃ ሣትታይ በጨለማ ጊዜ ከተከበረ ዓመቱ በሙሉ የመከራ፣ የችግርና የህመም ዘመን ይሆናል ተብሎ ስለሚታመን ቅዳሜ ዕለት መምረጥ የግድ ነው፡፡ የመስቀል በዓልን ሁሉም የብሔረሰቡ አባላት በደስታና በተድላ እንዲያሣልፉ ስለሚፈለግ ሁሉም የአቅሙን ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ያለው ለሌለው ከጥሬ ገንዘብ አንስቶ እስከ እርድ ከብት ድረስ በዱቤ /እባ መስጠት የተለመደ ባህላዊ ሥርዓት ደንብ ሲሆን፤ የዚህ ዕዳ /ገንዘብ/ በታህሳስና ጥር ወራት ይከፈላል፡፡
በመስቀል በዓል ጊዜ ያለው ሣምንት የአበባ ቀን /ዘራሮ በር/ ተብሎ ይጠራል። በዚህ ሣምንት ያሉ ቀናት የተለያዩ ተግባራትና ባህላዊ ሥርዓቶችን ለማከናወን የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ ቅዳሜ ዋናው የበዓሉ ዕለት ነው፡፡ ለመስቀል በዓል ብዙውን ጊዜ እርድ የሚፈፀመው በዚህ ቀን በመሆኑ ዕለቱ የእርድ ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ ከቅዳሜ በፊት ያለው ሐሙስ ቀን “ጩፎ ሀሙሳ፣ ሙዱላ” የሚባል ሲሆን በዚህ ዕለት የተቀለቡ ሠንጋዎች /ማንቹ/ ተገዝተው ይቀርባሉ፡፡
በጩፎ ሀሙሣ" ዕለት የበዓሉ ቀን የሚጠጣ ባህላዊ መጠጥ “ቦርዴ”፣ “ሴሎ” ወይንም ጠላ ይጠመቃል፡፡ ከ"ጩፎ ሙዱላ" አንድ ሣምንት አስቀድሞ የብሔረሰቡ ባህላዊ አስተዳደር መሪዎች “ኮሮፍራ” _ ወይም “ወማ” ወይም ታዋቂ የአገርሽማግሌዎች ገበያ ውስጥ በመገኘት ወይንም መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ነጋሪት በማስመታት የመስቀል ቀንን ያውጃሉ፤ እንዲሁም ለህዝቡ መልካም ምኞታቸውን ይገልፃሉ፡፡ በ'ጩፎ ሀሙሣ" ማግስት ያለው ዓርብ ቀን “ያክማ” ወይም የ”አተካኖ” ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ የእርድ ዕለት /ቅዳሜ/ የመጀመሪያው ሠንጋ የሚታረደው በባህላዊ መሪዎች /ኮሮፍራ፣ዋማ/ ወይም ታላላቅ ሰዎች ደጃፍ በመሆኑ ዝግጅቱ እዚያው ይደረጋል፡፡ የሚታረደው ከብት በቅርጫ መልክ የሚከፋፈል ሲሆን እያንዳንዱ ተቃራጭ ቡድን “ሼማቶጀ” በመባል ይጠራል፡፡ ለእርድ የተዘጋጀው ሠንጋ ሲቀርብ የቤቱ ባለቤት ቅቤና እርጥብ ሣራ በከብቱ ላይ ይቀባባል፤ ያሻል፤ ከቆጮ የተሠራውን ባህላዊ ምግብ በጀርባው ላይ በተን በተን ያደርጋል፣ ባህላዊ መጠጥና እርጥብ ሣር በእጁ እንደያዘ ይመረቃል፡፡
እሁድ ጠዋት ምግብ ከመበላቱ በፊት “ጨጵሻ” የሚባል ባህላዊ ሥርዓት የሚፈፀምበት ዕለት ነው፡፡ “የጨጵሻ” ሥርዓት ማለት አባት የሞተበት ሁሉ ወደ አባቱ መቃብር በመሄድ በመቃብሩ ላይ ትኩስ ወተትና ማር በእንሰት ቅጠል ጫፍ በመያዝ አያት ቅድመ አያቱን ተራ በተራ እየጠራ “አብራችሁ ብሉ ጠጡ” በማለት እያፈሰስ የሚፈፅመው ባህላዊ ሥርዓት ነው፡፡ በአባት መቃብር ላይ አፍሰው የቀረውን ጭላጭ ወንድ ልጅ ያልወለድክ አባት ይህን ጠጣ በማለት በእጃቸው ማዳፍ ላይ አድርገው ይረጫሉ። ማክሰኞ የ"አዋያ" ባህላዊ ሥርዓት መፈፀሚያ ዕለት ነው፡፡ በዕለቱ አባወራ ለአባቱ “አዋያ” በማለት ቅዳሜ የእርዱ ቀን ካመጣው የቅርጫ ሥጋና  ምግብ እንዲሁም ባህላዊ መጠጥ መላ ቤተሰቡ ከታላቅ ቤት ጀምሮ ተራ በተራ እየተዞረ የሚበላበትና የሚጠጣበት ቀን ነው
                                       ባህላዊ የቤት አሠራር
እስከ ፍፃሜው ድረስ የብሔረስቡ ባህላዊ የቤት አሠራር መሠረቱን ከመጣል ጀምሮ እስከ ያሉ ተግባራት በሙሉ የሚከናወኑት በህብረት /በደቦ/ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራው ቤት ግዲቹ” ወይም “ሁጉሞ ጠምባርቹ" በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ አሠራሩ ከላይ እስከ ታች በሣር የተሸፈነ ባለአንድ በር ቤት ነው፡፡

ባህላዊ ቤቱ ሲሠራ ለምሶሶ የሚመረጠው የዋንዛ" ወይም የ “ዶቅማ እንጨት ሲሆን ለግድግዳና ማገር የሚሆኑ “ሀመካ፣ ሀንጠዞ” የሚባሉ ቀጫጭን የጫካ እንጨቶች እንዲሁም “ጮልባና መኮሶ” የሚባል ከመሬት እስከ ምሶሶ ጫፍ የሚዘልቅ ረዣዥም እንጨቶች፣ እንዲሁም ግድግዳና ማገር ማሠሪያ ሀረግ “ጋሌ" በህብረት ተቆርጠው ይዘጋጃሉ፡፡ የቤቱን ምሶሶ ባለቤቱ ከመረጠ በኅላ የተመረጡ ሰዎች ተሰብስበው ምርቃትና ፀሎት ያደርሣሉ፤ ወዲያውኑ ባለቤቱ መቁረጥ እንደጀመረ ሌሎች ተረዳድተው ከጣሉ በኋላ “ሆ ሄሎ" የሚል ባህላዊ ጭፈራ እያስሙ ቤቱ ወደሚሠራበት ሥፍራ ያደርሳሉ፡፡ ምሶሶው ከመቆረጡ በፊት በጉድጓድ ውስጥ ጥላሸት፣ ጭድና አመድ፣ ጨውና ብቅል ይጨምራሉ፡፡

                                          ባህላዊ ምግቦች
የብሔረሰቡ ባህላዊ ምግቦች አዘገጃጀትና የአመጋገብ ሁኔታ በ "አዘቦትና" በ "በበዓል ቀናት" ተብለው በሁለት ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ በተለይ በበዓላትና በሠርግ ጊዜ ከሚዘጋጁ የምግብ ዓይነቶች መካከል ክትፎ፣ የጐመን ክትፎ /ዑላሞ/፣ ቆጭቆጮ /የበግና የፍየል ጠቦት ቅቅል/፣ ቡራቶ /በቅቤ የታሸ የገብስ ቆሎ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
                                       ባህላዊ አለባበስ
ቀደም ሲል በነበረው ባህላዊ አለባበስ ከቆዳና ከጥጥ የተሠሩ ባህላዊ ልብሶች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ወንዶች ከወገብ በታች ሳላንፌሎ፣ አስራ፣ ጠጠባ ይለብሳሉ፡፡ ጠጠባ ወይንም መቀነት በመባል የሚታወቀው የተራ ሰው እና የጀግና /የዘማች/ተብሎ በሁለት የሚከፈል ሲሆን መጠኑና አለባበሉ ይለያያል፡፡ በወገቡ ላይ እስከ 20ክንድ የሚደርስ_ ጠጠባ /መቀነት/ እንዲሁም ከወገቡ በላይ አኮና ወይም መርጣ የሚባል ባህላዊ ልብስ ይደርባል፡፡ "መርጣ" ባህላዊ ልብስ ይደርባል፡፡ “መርጣ" ለወንዶችም ሴቶችም ያገለግላል፡፡ ሴቶች ከወገብ በታች ከመቀነት ጋር ለብሰው “ክታ” ይደርባሉ፤ ታዋቂ ሴቶች ደግሞ “አኮና" የሚባለውን ከወገብ በታች ይለብሣሉ፡፡ ህፃናትና ታዳጊዎች “ለንዳ የሚባለውን ባህላዊ ልብስ ይለብሳሉ፤ ዎመሽኮ” የሚባል በማሰር ሐፍረተ ሥጋቸውን ይሸፍናሉ፡፡ የተለያዩ ጨሌዎችን፣ ዶቃዎችን፣ ጥለትን፣ የብርና የነሐስ ውጤቶችን ከጥጥና ከቆዳ የተሠሩ ልብሶች ላይ በማድረግ ለጌጣጌጥ ይጠቀማሉ፡፡
                                                    ባህላዊ የለቅሶ ሥርዓት
በብሔረሰቡ ባህልና ወግ መሠረት በተለይ ታዋቂ ሰዎችና የዕድሜ ባለፀጋዎች ሲሞቱ የተለያዩ ባህላዊ ሥርዓቶች ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡ የሟች የቀብር ሥነ-ሥርዓት የሚፈፀመው ሟች በህይወት ዘመኑ ባለው የሀብት መጠንና ዘመድ አዝማድ ብዛት ጊዜ ተወስዶ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የሟች ዘመዶች በተለያዩ ቦታ የሚገኙ ከሆነ ለቅሶ ሳይለቀስ በድብቅ እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ በአካባቢ ያሉ የሀገር ሽማግሌዎች በመገናኘት የቀብሩን ዕለት ይወስናሉ፡፡ ለቅርብ ዘመድ አዝማድ መልዕክት መተላለፉ ይረጋገጣል፤ መልዕክቱ የደረሳቸው ዘመዶች እህል ጭነው፣ ከብት ይዘው ለለቅሶ ይመጣሉ፡፡ ከቀብሩ ዕለት በፊት ለለቀስተኛው ከብት ይታረዳል፤ ድግስ ይደገሣል፡፡ የሟች የበኩር ልጅ በተለይም ወንድ ልጅ አስከሬኑ የሚያርፍበትን ጉድጓድ ቦታ በቅድሚያ እንዲወጋ ይደረጋል።ይህንንም ባህላዊ ደንብ በመፈጸሙ በባህሉ መሠረት ከአባቱ ንብረት የሚፈልገውን መርጦ እንዲወስድ ይደረጋል፡፡ ሥርዓተ ቀብሩ በተፈፀመ በሶስተኛው ቀን በብሔረሰቡ ባህል መሠረት የራስጌ ነገር ወይንም “እርጃሜናአንሻጣ ጋባአ" የሚባል ባህላዊ ደንብ ይፈፅማሉ፡፡ በግ ይታረዳል፤ ቤተሰብና የቅርብ ዘመድ አዝማድ ለሀዘን መግለጫ ፀጉሩን ይላጫል፤ የለቅሶ ቤት እንዲፀዳ፣ እንዲጠረግ ይደረጋል፡፡

ከተወሰኑ ቀናት በኋላ “መቃብር ማንሣት” የሚባል ባህላዊ ሥርዓት አስከሬኑ በተቀበረበት ሥፍራ ይካሄዳል፡፡ አፈር በመቃብሩ ላይ በልዩ ሁኔታ ከፍ ተደርጐ እንዲቀመጥ ይደረጋል፣ ለምልክትነት ዛፍ ይተከላል፣ በሬ ይታረዳል፡፡ የታረደው በሬ ትኩስ ደም ከትኩስ ወተት ጋር ተቀላቅሎ በመቃብሩ ላይ እንዲፈስ ይደረጋል፡፡ በብሔረሰቡ እምነት መሠረት ይህ “ነፍስ ትቀዝቅዝ'' ማለት ነው፡፡
ይህ እንደተፈፀመ ከጥቂት ቀናት በኋላ “ቦአ" የሚባል ባህላዊ የተዝካር ሥነ-ሥርዓት ይከናወናል፡፡ በ'ቦአ" ሥነ-ሥርዓት ላይ የሟችን የጀንግነት ውሎ ለመግለፅ በቀንድ ዋንጫ፣ ማር እየተቀዳ የሟች የዕድሜ አኩያዎችና ዝናውን መግለፅ የሚችሉ ሰዎች "ኬሶ" እያሉ እየተወራረዱ በቀረርቶና በፉከራ መልክ የህይወት ታሪኩን ይገልፃሉ፣ ይህ ባህላዊ ስርዓት ከተፈፀመ በኋላ የቀብሩ ፍፃሜ ይሆናል፡፡