Skip to main content

ሀላባ

                                                        የሀላባ ዞን አጠቃላይ ገጽታ
የሀላባ ዞን በክልሉ ከሚገኙት 7 ዞኖች መካከል አንዱ ሲሆን የዞኑ ዋና ከተማ “ቁሊቶ ትባላለች፡፡ ቁሊቶ ማለት "ናፈቀኝ" ማለት እንደሆነ ከብሔረሰቡ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በ1999 ዓ/ም የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት መሠረትና ፕላን እና ልማት ቢሮ 2017 ዓ.ም ፕሮጄክሽን ወንድ 171,662 ሴት 165,567 ድምር 337,230 እንደሚሆን ይገመታል፡፡ 
ዞኑ በስሜን ከሥልጤ፣ በደቡብ ከሀዲያ፣ በምዕራብ ከከምባታ  ዞኖችና በምሥራቅ ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ይዋሰናል፡፡ አጠቃላይ የቆዳ ስፋቱ 855 ስኩዌርኪ.ሜ ነው፡፡ መልከአ ምድሪ ዊ አቀማመጡ 70% ሜዳማ ፣ 27% ተዳፋት 3% ተራራማ ሲሆን የአየር ንብረቱም ከ8ዐ% ወይና ደጋ ቀሪው ደግሞ ቆላማ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በዞኑ በስፋት ከሚመረተው በርበሬ በተጨማሪ ማሽላ፣ ጠ.ፍ፣ ገብስና ስንዴ ይመረታል። 
                                                                       የሀላባ ብሄረሰብ
ሀላባ የተሰኘዉ የብሔረሰቡ መጠሪያ ከሄላዊ ኮረብታ (ባሌ ውስጥ የሚገኝ) የተወረሰ ስለመሆኑ የተለያዩ ፅሑፎችና የብሔረሰቡ ትውፊቶች ያመለክታሉ፡፡ የብሔረሰቡ አባላት በአሁኑ ጊዜ በዋናነት ከሚኖርበት  የሀላባ ዞን ውጪ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ፣ በጅማ፣በባሌ እንዲሁም በደቡብ ክልል በጉራጌ፣ በካምባታ ጣምባሮ፣በሀዲያ፣ ስልጤና ሲዳማ ዞኖች በርከት ብሎ እንደሚኖር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የሀላባ ብሔረሰብ ቋንቋ ሀላቢሣ ከኩሽቲክ ቋንቋ ቤተሰብ ይመደባል፡፡ ሀላቢሣ ከደጋማው የምስራቅ ኩሻዊ (High land east Cushitic) ቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ ከቀቤንኛ፣ ሲዳሙ አፎ፣ ካምባትሣ፣ ጣምባርሣና ሃዲይኛ ጋርየ መመሳሰል ባህሪይ አለው፡፡ ለዚህም ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች የሚሰጡት ምክንያት ታሪካዊ አመጣጣቸው ከአንድ አካባቢ መሆኑና አሁንም አጐራባቾች ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ፡፡ ቋንቋውን ለማሳደግ የተወሰኑ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ለአብነትም አንግሊዝኛ-አላብኛ መዝገበ-ቃላት እና “የጀርመንና-አንግሊዝኛ-ሀላብሳ መዝገበ- ቃላት"፣የሀላብሣ ቋንቋን የትምህርት መስጫ ቋንቋ ለማድረግ የሚረዳ አጋዥ መጽሃፍ (Halabisa Grammer, phonoilogy, Morphology and Syntax) በብሔረሰቦች ም/ቤት ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ ውሏል። በተጨማሪም በቋንቋው በአንደኛ ደረጃ የመጀመሪያ ሳይክል ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በብሔረሰቡ ከአፍ መፍቻ ቋንቋው በተጨማሪ አማርኛ፣ ስልጢኛ፣ ኦሮሚፋ፣ ከምባትሣና ሀዲይሳ ቋንቋዎች በሰፊው የሚነገሩ ናቸው፡፡
                                                                     የብሄረሰቡ ታሪካዊ አመጣጥ
ሀላባዎች ከአረቢያ በመነሣት ቀይ ባህርን አቋርጠው በዘይላ በኩል ምስራት ኢትዮጵያ ገብተው ለ70 ዓመታት ያህል በዚያው ሰፍረው ክቆዩ በኋላ ክነባር ነዋሪዎች ጋር ባለመስማማታቸው የሰፈሩበትን አካባቢ ለቀው ወደ አርሲ እንደገቡ የተለያዩ ፀሐፍት የራሳቸው መላምት አሏቸው። ኘሮፌስር ታደሰ ታምራት በ1979 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፋቸው በገፅ 126 ላይ "የአላባና ቀቤና” /አላባ ቀቤና ገራድ/ ጥንታዊ ዝርያቸው ከሴም ዝርያ ክሆኑ ክደቡብ አረቢያ በመነሣት የዘይላን ወደብ በማቋረጥ ወደ ሐረር በመንቀሳቀስ ከ300-1000 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሐረር አካባቢ እንደሰፈሩ ይጠቅሳሉ፡፡
ከላይ የተገለጸዉን ሃሳብ የሀላባ አዛውንቶች የሚስማሙበት ሆኖ ሀላባዎች ከአረቢያ ከመጡ በኋላ ወደ አረብ ሀገር በንግድ ሥራ እየተንቀሳቀሱ ለረጅም ዓመታት የኖሩ ቢሆንም በምሥራቅ ኢትዮጵያ /ሐረር/ አካባቢ በተከሰቱ ጦርነቶች ሳቢያ ቦታውን በመልቀቅ ወደ ተራራማ አካባቢ አዲስ ኑሮ እየመሠረቱ ቀስ በቀስ ወደ ምዕራብና ደቡብ አቅጣጫ በመንቀሳቀስ በሲዳማ አካባቢ ልዩ ስሙ "ጉጉማ" የሚባል ቦታን አቋርጠው ወደ ዛሬው አርሲ፣ ባሌና ሲዳማ አዋሣኝ ደጋማ መሬት ላይ ሠፍረው እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ሀላባዎች ከሐረር ተነስተው አሁን የሚገኙበት አካባቢ በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን እስከሠፈሩ ድረስ ሦስት ትውልድ አንዳለፈ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
                                                            ባህላዊ አስተዳደር
ብሄረሰቡ በነባር ባህሉ የራሱ የሆነ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት አለው፡፡ ብሔረሰቡ የሚተዳደርበት ሕግ “ሴራ” ሲባል ሕዝቡም ለባህላዊ ሴራ ተገዥ ሆኖ ይመራል፡፡ ባህላዊ መተዳደሪያ ሥርዓቱ "ሴሪዳኞማት ይባላል። ሴራው የየራሳቸው የሆነ መጠሪያ ያላቸው የሥልጣን አካላት አለት፡፡ ብሔረሰቡን የሚያስተዳድሩት የጎሣ መሪዎች ሲሆኑ በሀገር ጉዳይና በሕልውና ላይ የመጣ ችግር ካለ ብቻ በመሰባሰብ ይፈታሉ፡፡ የዚህ የባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት ከፍተኛው አካል ጠቅላላ ጉባዔ ወይንም ሸንጎ ነው፡፡ ይህ ሸንጎ በብሔረሰቡ አጠራር “ኦጋቴ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን የመሰብሰቢያ ቦታው ጥላ ስር ነበር። የስብሰባው መሪ “ወማ” ይባላል። በወማ ስብስባ የሚሰጥ ውሣኔ የመጨረሻ ይሆናል፡፡ በየጐሣው ያሉ የጐሣ መሪዎች በብሔረሰቡ አጠራር “ቦክ ሙሪቾ" በመባል ሲታወቁ ጎሣውን የሚመሪው “ዳቦ ሙሪቾ" ይባላል፡፡ እነዚህ መሪዎች በኦጋቴ /ሽንጐ/ ሥር ሆነው የቤተሰቡንና ጐሣውን አስተዳደራዊ ሥራዎች የሚሠሩ ናቸው፡፡ አጠቃላይ ስብሰባ /ኦጋቴ/ ሲኖር ኦጋቴን የሚመራው የ”ሲዴ" ጐሣ ነው፡፡ ምክንያቱም በብሔረሰቡ የሲዴ ጐሣ አባላት የነብዩ መሐመድ ዝርያ ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ የየጐሣዎቹ ጉባዔ የሚመራው ግን በጐሣ መሪዎቹ ነው፡፡
የጎሣ መሪነት ስልጣን በዘር ሀረግ የሚተላለፍ ሆኖ የሥልጣን እርከናቸው የሚወሰነው ግን በግርዘት ሥርዓት ቅደም ተከተላቸው መሠረት ነው፡፡ ግርዘኞች ቁስላቸው መድረቅ ሲጀምር ለስድስት ወራት በዋርካ /ግራር/ ስር ተሰብስበው ለግርዘኞቹ ስም የሚያወጡበት ባህላዊ ሥርዓት /ነቃታ/ ላይ በሚያሳልፉት ቆይታ ቤተሰብና አገርን እንዴት መምራትና ማስተዳደር እንዳለባቸው ሰፊ እውቀትና ግንዛቤ የሚያገኙበት ሥርዓት ነው፡፡ ወደ “ነቃታ” ሄዶ ሲዴ ላይ ምልክት በማድረግ ስብሰባውን የመምራት ክህሎት ያገኛል፡፡ በቀጣይም ስብሰባዉን የመምራት ኃላፊነት ይሰጠዋል።
ከአጎራባች ብሔረሰቦች ጋርም ሆነ በብሔረሰቡ አባላት መካከል ለግጭት መንስዔ የሚሆኑት የግጦሽ መሬት ጥያቄ፣ በዝርፊያም ሆነ በጋብቻ ምክንያት የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ናቸው፡፡ ከቀደምት ጊዜያትም ሆነ አሁን ከአጎራባች ብሔረሰቦች ጋር የሚፈጠረው ግጭት ከሁለቱም ወገን በተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች አማካኝነት በሰላማዊ መንገድ ይፈታል፡፡ በሀላባዎች ባህል ሌላው ብሔረሰብ እንዳይበደል ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ በብሔረሰቡ ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት በዳይ ተበዳዩን እንዲክስ ይወሰንበታል። የቅጣቱ መጠን እንደ ጥፋቱ ዓይነት የሚወሰን ሆኖ ጥፋተኛው በገንዘብና በዓይነት ለተበዳዩ ኮርማና ማር እንዲክስ ይደረጋል፡፡
በብሔረስቡ እንደ ከባድ ጥፋት የሚታየው በዳዩ የተበየነበትን የቅጣት ውሳኔ ሳያከብር የቀረ እንደሆነ ነው፡፡ በዳይ የተበየነበትን ቅጣት አልከፍልም ካለና የሽማግሌ ውሣኔ ካልተቀበለ የጐሣ መሪው ፊት ቀርቦ እንዲዳኝ ይደረጋል። የጐሣ መሪውን ውሣኔ ካልተቀበለ የመጨረሻ ቅጣት ይጣልበታል፡፡ የመጨረሻው የቅጣት ውሣኔ.ም ከቤተሰቡና ከጐሣ እንዲገለል፣ የአካባቢው ሕዝብ በበዳዩ ደስታና ሃዘን ላይእንዳይደርሱ፣ ቢቸገር አንዳይረዱት፣ በአጠቃላይም፣ ከጐሣውም ሆነ ከአካባቢው እንዲገለል ይደረጋል። እንዲህ ዓይነት ጥፋትና ቅጣት የተጣለበት ሰው በጥፋቱ ተፀዕቶ በዳዩን ከካሰና ከተቀጣ በኋላ የጐሣ መሪውንና ቤተ ዘመዱን ይሁንታ ካገኘ ብቻ የመጨረሻ ዕርቅ ይሆናል፡፡


ለእርቅ ማር የመርጨት ዝግጅት በሀላባ ብሔረሰብ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት የሴቶች የወሣኝነት ሚና የተገደበ በመሆኑ አብረው ሸንጎ አይቀመጡም፡፡ ይሁንና ግጭቶች ተፈጥረው ጉዳዩ በዕርቅ ሲፈፀም ሴቶች በምርቃት ሥርዓቱ ላይ ይሳተፋሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ያለ ሴት ምርታት ውሣኔው አይፀናም ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ በነፍስ ግድያ የጉማ ዕርቅ ረጋ/ ሲፈፀም ማር ረጭታ የምታስታርቀው ሴት ናት፡፡ ሴት ልጅ በደል ደርሶባት ለሸንጐ አቤቱታ ካቀረበች በአስቸኳይ ውሣኔ ተሰጥቷት እንድትካስ ይደረጋል፡፡
                                                ባህላዊ እሴቶች
በሀላባ ብሔረሰብ ኃይማኖታዊ /መንፈሣዊ/ ሥርዓት የሚመራው በኢማሞች ነው፡፡ በአብዛኛው የብሔረሰቡ አባላት ሙስሊሞች በመሆናቸው የእስልምናን የኃይማኖት ሥርዓት ይከተላሉ፡፡
                                                የጋብቻ ሥርዓት
ጋብቻ በሀላባ ብሔረሰብ ትልቅ ግምት ከሚሰጣቸው ባህላዊ እሴቶች አንዱ ነው፡፡ በብሔረሰቡ ስድስት ባህላዊ የጋብቻ ዓይነቶች አሉ። እነዚህም ቀጥተኛ ጋብቻ /መኢሲሶ/፣ ቀበቶ መስጠት ጋብቻ፣ /ቡሬንአስ/፣ ማስኮብለል ጋብቻ /ሄረና/፣ ጠለፋ ጋብቻ /ጎሱ/፣ የድንገት ጋብቻ ወጋ-ቢላሬቡታ፣ የውርስ ጋብቻ /አጋ/ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ጋብቻ ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ የራሱ ሥርዓትና ሂደት አለው፡፡
የቀጥተኛ ጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓት የሚጀምረው "ወፍ ማየት" /ጩቹ ለኢ/ በሚለው ነው፡፡ የሚያገባው ወጣት ከጓደኛው ጋር ልጅቱ ቤት ይሄዳል፡፡ በመቀጠል አባቱ በህይወት ካለ ከአባቱ ጋር አባቱ በህይወት ከሌለ ከሌላ ሽማግሌ ጋር በመሆን ይሄዱና ወፍ ማየት በሚለው ሕጋዊ ሥርዓት የወደፊት እድላቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ወደ ልጅቱ ቤት በሚመላለሱበት ጊዜ በሚጠጣበትና በሚበላበት ጊዜ ከደረሱ፣ መንገድ ላይ ውኃ ቀድታ የምትመለስ ሴት ካጋጠማቸው ልጅቱ ገዳም ነች ተብሎ ስለሚታመን ሽማግሌ ይላክና ይሁንታ ሲገኝ ጥሎሽ ይሰጣል፡፡ ጥሎሹ ኒካ /ቃል ማሰሪያ/ በሚል የሙስሊምን ህግ ተከትሎ ይፈፀማል፡፡ ብዙ ውጣ ውረድ ሳይኖርአጀብ ወይም ቤተዘመድ ሳይበዛ በሚደረግ ሥርዓት የሚፀና ጋብቻ ነው፡፡ ከቤተሰብ እውቅና ውጭ ሁለቱ ተጋቢዎች ተፋቅረው ወይም ልጅቱን በማባበል ይወስድና ለቤተሰቧ ሽማግሌ ተልኮ በእርቅ የሚያልቅ ነው፡፡ የጠለፋ ጋብቻ ከቤተሰብና ከልጅቱ ፍቃድ ውጭ በማስገደድ የሚፈፀም ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች እጮኛውን ያጣ /በሌላ የተነጠቀ/ ወጣት ከእጮኛው ቤተዘመድም ይሁን ከሌላ ቤተሰብ በድንገት በመጠየቅ የሚፈፀመው ጋብቻ የድንገት ጋብቻ /ወጋ ቢላሬቡታ/ በመባል ይታወቃል፡፡
በሀላባ ብሔረሰብ ባሏ የሞተባትን ሴት የባል ወንድም ወይም ከቤተዘመድ የተፈቀደለት የሟችን ሚስት በመውረስ ማግባት የተለመደ ነው፡፡ በዚህ ጋብቻሥርዓት ሴቷ ቤተዘመድ መርጦ ያቀረበላትን ወንድ በባልነት ከመቀበል ውጭመቃወም አትችልም። ሌላው አንድ ሴት የወደደችውን ልጅ ቤተሰብ ቤት በድንገት ገብታ ወድጄ እዚህ ገብቻለሁና ከዚህ ቤት አታውጡኝ ብላ የቤቱን ምሶሶ በማቀፍ የምትፈፅመው ጋብቻ ነው፡፡
በሀላባ ብሔረሰብ የግርዘት ሥርዓት ከጥንት ጀምሮ በሁለቱም ፆታዎች ላይ በእኩል ይፈፀማል፡፡ በባህሉ መሠረት የልጆች የግርዘት ዕድሜ ከ8 ዓመት በላይ ሲሆን ግርዘቱ የሚፈፀመው ትዳር ከመመስረታቸው በፊት ነው፡፡ ግርዘኞች ለመገረዝ እንድ ቀን ሲቀራቸዉ የሀበሻ ኮሶ ይጠጡና የጠጡበትን ዕቃ በጭንቅላታቸው አዙረው በመስበር ሲጨፍሩ አድረው ጧት ይገረዛሉ፡፡ ቁስላቸው መድረቅ ሲጀምር ወንዶችም ሴቶችም በትልቅ ዋርካ ወይም ግራር ሥር በመሰባሰብ ከመካከላቸው በመረጡት መሪ አማካይነት ለሁሉም ስም በማውጣት ሥርዓቱ ያበቃል፡፡
                                            ባህላዊ በዓላትና ጨዋታዎች
ብሔረሰቡ በደስታ በጥጋብና በሥራ ጊዜ የሚዘወተሩ ባህላዊ ጨዋታዎች ያሉት ሲሆን የጨዋታው ዓይነት በፆታና በዕድሜ ይወሰናል፡፡ እረኞች /ሁዌ ገዶ ሁዌው ሲጫወቱ፤ በሴቶች ግርዘት ወቅት ወንዶች “ሆይ ሎሌ ሎሌ”ን ይጫወታሉ፣ በወጣት ወንዶች እና ሴቶች የሚዘፈኑ የሠርግ ዘፈኖች ፣ የአዝመራ ጊዜ፣ ለፉከራና ለሙገሣ የሚዘፈኑ ዘፈኞቹ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከበሮና ዋሽንትም ዋነኛ የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸው ናቸው፡፡
በብሔረሰቡ ዘንድ ከባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት ባልተናነሰ መልኩ የባህላዊ እምነት ሥነ-ሥርዓት ተዘውትሮ ይካሄድ እንደነበር ይነገራል፡፡ በክርስትና ኃይማኖት መስፋፋት የተነሣ እየቀረ መጥቷል እንጂ ቀደም ሲል የተወሰነው የማህበረሰቡ ክፍል የቀይዳራ" /የቃልቻ/ ወይንም “ዋዕማንቾ" እምነት ተከታዮች እነደነበሩ ይነገራል፡፡ የዚህ ልማዳዊ እምነት ተከታይ የሆኑ በሙሉ “ቃይደራ" የሚባለው አንድ የተለየ ኃይል ያለው የሁሉም አምላክ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ይህም አምላካቸው የመላውን ህዝብ ህይወት በቅርበት እንደሚከታተል እና ከጠላት፣ ከረሀብ፣ ከበሽታ፣ ክእርዛት…ወዘተ እንደሚጠብቃቸው ስለሚያምኑ ያክብሩታል፤ ወጉንም በሚገባ ይጠብቁታል፡፡ ይህ ካልተፈፀመና ተግባራዊ ካልተደረገ ቆሌው ይቆጣል፤ በዚህም የተነሣ ለቅጣት ብሎ በበሽታ ወረርሽኝ የማዝመት፤ በረሀብና እርዛት የማሰቃየት፣ በአጠቃላይ የቁም ስቃይ የማሳየት ኃይል አለው ስለሚባል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ሥፍራና ግምት ይሠጠዋል። በመሆኑም የ”ቃይዳራ” እምነት ተከታዮች ከእርሻ ምርታቸውና ከሚያረቡት ከብቶቻቸው በሩን ለቀይደራ" ይሰጣሉ፡፡ በመስቀል በዓል ጊዜም ለአባታቸው አያቶቻቸው የሙት መንፈስ መስዋዕት ያቀርባሉ፡፡
                                              የአመጋገብ እና አለባበስ ሥርዓት
በብሔረሰቡ የአመጋገብ ሥርዓት ሴት ልጅ ከወላጅ ጋር አብራ እንድትበላ ባህሉ አይፈቅድላትም፡፡ ባህላዊ አለባበስ በፆታና በዕድሜ ይወሰናል። አዛውንቶች ጋቢ፣ ቡልኮ፣ /በቅቤ የተነከረ/ ኮት፤ ተነፋነፍ ሱሪ፣ ጉፍታ እና ጥምጣም አድርገው አለንጋ ይይዛሉ፡፡ ሴቶች ከናይለን ጨርቅ የተስፋ ቀሚስ ልዩ ልዩ ቀለምና መጠን ባላቸው ቁልፎች ልብሳቸውን ያስጌጣሉ፡፡ ወገባቸውን በመቀነት ይታጠቃሉ፡፡ የተለያየ የፀጉርአሠራርም አላቸው፡፡ ወጣቶች እጀ ጉርድ ሸሚዝና ቁምጣ ላይ የተለያዩ ቁልፎችን በማንጠልጠል ያስጌጡና ሰደርያ ደርበው በመልበስ አሰንደዶና አክርማ የተሠራ ባርኔጣ ያደርጋሉ፡፡
                                                ቤት አሠራር
የሀላባዎች ባህላዊ ቤት ክብ ሆኖ ጣራው ከስንደዶ ሣር ይከደናል፡፡ ቤት ሠርቶ ከድኖ ማጠናቀቅ የወንዶች ሲሆን ሴቶች ምርጊቱንና ውስጡን የመደልደል ሥራ ይሠራሉ፡፡ ሀላባዎች ከሽክላ፣ ከእንጨት፣ ከብረት፣ ከሰንደዶና አክርማ የሚሠሯቸው የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች እና የእርሻ መሣሪያዎች አሏቸው፡፡ ከአነዚህ ሌላ ከጥጥ የሚሠሩ አልባሳት፣ ከእንስት ተዋጽኦ የሚሠሩ የመኝታ ዕቃዎች እና የተለያዩ ባህላዊ የጦር መሣሪያዎችንም ያመርታሉ፡፡


                                የለቅሶና የሐዘን ሥነ-ሥርዓት
በሀላባ ብሔረሰብ ጀግና ወይም የጐሣ መሪ ሲሞት ይገለገልበት የነበራቸው ዕቃዎችና አልባሳትን በመያዝ ይለቀሳል፡፡ ሴቶች በጥፍራቸው ፊታቸውን እየቧጨሩ ያለቅሳሉ፡፡ ይሁንና በሐይማኖታዊ ሥርዓት የተከለከለ በመሆኑ ቀብር ቦታ አይሄዱም፡፡