Skip to main content

የምክር ቤቱ አመሰራረት

የቀድሞ ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ዉስጥ አብረውን የነበሩ የሲዳማ ብሔር፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች እና የደቡብ ኢትየጵያ ህዝቦች የራሳቸዉን ክልል ለመመስረት ባላቸዉ ህገ መንግስታዊ መብት በመጠቀም በህዝበ ዉሳኔ በክልል የመደራጀት መብታቸውን ያረጋገጡ በመሆኑ፣ የቀረው የክልል አደረጃጀት አስቀድሞ ከነበረው የክልሉ ስያሜ፣ ከአስተዳደራዊ ወሰን፣ ርዕሰ ከተማ፣ ዓርማና ሰንደቅ ዓላማ፣ ከመልክዓ ምድራዊ አሰፋፈር እና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች አንፃር መሰረታዊ ለዉጦች የተከሰቱ በመሆኑ፣ ከእነዚህ ለውጦች አንጻር በመቃኘት ለማጣጣምና ለማስተካከል እንዲቻል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአዲስ መልክ በማደራጃት አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ላይ በመደረሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስትን የመሰረቱት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በተወካዮቻቸው አማካይነት ነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ሕገ መንግስት መጽደቃቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በክልሉ ህገ መንግስት አንቀጽ 52 መሰረት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ም/ቤት መስከረም 5/2016 ሳጃ ከተማ ተመሰርቷል  ፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያሏት፣ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮች፣ እምነቶች እንዲሁም እምቅ በሆኑ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች የታደለችና በጥንት ስልጣኔዋ የምትታወቅ ሀገር ናት፡፡ ከነዚህም ብሔረሰቦች ውስጥ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስትን በጋራ፣ በአንድነት፣ በመፈቃቀድ እና ተስማምተው የመሰረቷት 10ሩም ነባር ብሔረሰቦች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ አዲሷ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እጅግ የሚያስደምሙ የተለያዩ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ታሪኮች እንዲሁም የተለያዩ የአኗኗር ዘዬ ያላቸው የአስደናቂ እሴቶች ባለቤት ብቻም ሣትሆን ከሌሎች በሀገራችን በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር ለዘመናት ተቻችለው፣ ተከባብረውና ተፈቃቅረው ሲኖሩ የነበሩና አሁንም በመኖር ላይ የሚገኙ ህዝቦች ያሏት የሁሉም መኖሪያ የብዝሀነት ምሳሌ የሆነች ክልል ናት፡፡ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ከተመሰረተ ቅርብ ጊዜ ቢሆንም በእነዚህ አጭር ጊዜያቶች ውስጥ በርካታ አመርቂ የሆኑ ተግባራቶችን መፈጸሙ ይታወቃል፡፡